ሰኔ ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በእነ አንዱዓለም አራጌ የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው፣ የከፍተኛው ፍርድ ቤት መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ አሰናብቷቸው የነበሩ አራት ተከሳሾች ላይ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከ10 እስከ እድሜ ልክ የሚደርስ የቅጣት ውሳኔ ዛሬ አሳለፈ።
የመንግስት አቃቤ ሕግ ብርሃኑ ወንድምአገኝ በነኚሁ አራት ግለሰቦች ላይ፣ ማለትም በ21ኛው ተከሳሽ ኮሎኔል አለበል አማረ፣ በ12ኛ ተከሳሽ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ፤ በ19ኛው ተከሳሽ አቶ ኤልያስ ሞላ እና በ20ኛው ተከሳሽ አቶ ደሳለኝ አራጌ ላይ ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው ተከሳሾቹ የተወነጀሉት ከግንቦት 7 ፓርቲ ጋር ግንኙነት በመፍጠር የሽብር ተግባርን ለመፈጸም በማቀዳቸው እንደሆነ ይጠቅሳል።
ምንም እንኳን የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥር 15 ፣ 2004 ዓ.ም ባስቻለው ችሎት፣ አቃቤ ሕግ ክሱን የሚያስረዱለትን ማስረጃዎች አላቀረበም በሚል በነፃ ቢያሰናብታቸውም፣ አቃቤ ሕግ ውሳኔው አግባብ አይደለም በማለት ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበው ይግባኝ ተቀባይነት አግኝቶ ተከሳሾቹ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሊተላለፍባቸው በቅቷል።
“ በሃገሪቱ የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ፣ በሚዲያ ተቋማትና በባለስልጣናት ላይ አደጋን ለመጣል ማሴራቸው በማስረጃ ሙሉ በሙሉ ተረጋግጧል” ያለው ፍርድ ቤት በመጨረሻ ባሳለፈው ውሳኔ 12ኛው ተከሳሽ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ በግንቦት ሰባት ውስጥ በአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት እንዲሁም የዲፕሎማሲ ሃላፊ መሆኑ ተረጋግጧል በሚል እጃቸው ከተያዘበት እለት ጀምሮ በ25 ዓመት ዕኑ እስራት 19ኛው ተከሳሽ አቶ ኤልያስ ሞላ እና 20ኛው ተከሳሽ ደሳለኝ አራጌ የግንቦት 7 አባላት ሆነው በመገኘታቸው እያንዳንዳቸው በ10 ዓመት ዕኑ እስራት፤ እንዲሁም 21ኛው ተከሳሽ ኮረኔል አለበል አማረ ደግሞ በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል።
አቃቤ ሕግ ብርሃኑ ወንድምአገኝ በነዚህ ተከሳሾች ላይ ያቀረበውን ክስ የሚያስረዳለት፣ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ማስረጃ ሳይኖር እንዲህ አይነት የተዛባ ውሳኔ መተላለፉ፣ ፍርድ ቤቶች ነፃ እንዳልሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የፍትሕ ስርዓት በአገራችን ምን ያህል እንደዘቀጠ ያመላከተ ሆኖ ተገኝቷል።
እነኚህ በሌሉበት ቅጣቱ የተላለፈባቸው አራቱም ተከሳሾች የሚኖሩት በውጭ አገር ሲሆን፤ ከነርሱም መካከል ኮሎኔል አለበል አማረና አቶ አፍሬም ማዴቦ፣ ከዓመት በፊት የህወሀት ኢህአዴግን ስርዓት በኃይል ለመጣል ሲንቀሳቀሱ ተደርሰባቸዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸው፣ በእስር ቤት ከሚገኙት ከእነ ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ ጋር በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸው ነበር።
የከፍተኛው ፍርድ ቤት፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በእነአንዷለም አራጌ የክስ መዝገብ የተከሰሱት ሌሎቹ ተከሳሾች ላይ የቅጣት ውሳኔ ለማስተላለፍ ለሐምሌ 6 ቀን 2004 ዓ.ም. ቀጠሮ መያዙ ይታወቃል።
አቃቢ ህግ በአቶ አንዱአለም አራጌ ፣ በዶ/ር ብርሀኑ ነጋ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ እና በአቶ ፋሲል የኔአለም ላይ ቅጣቱ ከብዶ እንዲተላለፍ ጥያቄ ማቅረቡን ፍትህ ጋዜጣ መዘገቡ ይታወሳል። አቃቢ ህግ ጥያቄውን ያቀረበው ግለሰቦቹ ተደጋጋሚ ጥፋት ያለባቸው በመሆናቸው እና ሊታረሙ ባለመቻላቸው ነው ብሎአል።
ከፍተኛው ፍርድ ቤት በእነ አንዱአለም አራጌ መዝገብ በተከሰሱት ላይ በቅርቡ ያስተላለፈውን የጥፋተኝነት ውሳኔ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት፣ ሲፒጄ፣ ሁማን ራይትስ ወችና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ማውገዛቸው ይታወቃል በማለት ቅዱስ ሀብት በላቸው ከአውስትራሊያ ዘግቧል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide