ሙስሊሙ ኢትዮጵያዊ የመንግስትን አካሄድ እየተቃወመ ነው

ሰኔ ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የመብት ጥያቄያቸውን እጅግ ሰላማዊ በሆነ መንገድ በማቅረብ ያለፉትን ስድስት ወራት ያሳለፉት ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ፣ መንግስት ጥያቄያቸውን ወደ ጎን በማለት አጠቃላይ ሂደቱን እሱ በሚፈልገው መንገድ ለማስተናገድ መሞከሩ ሙስሊሙን እያስቆጣ ነው።

በትናንት የአርብ ጁምዓ ጸሎት በአንዋር መስኪድ እና ፒያሳ በሚገኘው ኑር መስጊድ የተሰባሰቡ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን መንግስት ያቀረቡትን የመብት ጥያቄ ለማስተናገድ እየተጓዘበት ያለው መንገድ ችግሩን ከማወሳሰብ በስተቀር የሚፈይደው ነገር የለም።

መንግስት በአወልያ ተጀምሮ በመላው አገሪቱ እየተስፋፋ ያለውን ተቃውሞ  ከመብት ጥያቄነት አውርዶ የሽብረተኝነት ካባ ለማላበስ በሚመስል መልኩ ፣ የገዢው ፓርቲ ልሳን በሆነው ኢቲቪ “አንድ ሀገር ብዙ ሀይማኖት” የሚል የዶኩመንታሪ ፊልም አዘጋጅቶ ማሰራጨቱን ሙስሊሙ አጥብቆ ተቃውሟል።

ምእመናኑ “ኢቲቪ ውሸታም፣ ኢቲቪ የውሸት መፈልፈያ፣ እውነት የራቀው ቴሌቪዥን፣ ኢቲቪ የመንግስት ሎሌ ”  የሚሉ መፈክሮችን በማሰማት  የመንግስት ተቋማትን ማውገዛቸው ታውቋል። የምእመኑ የእስከዛሬ ተቃውሞ በአንድ ወይም በሁለት የመንግስት ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠረ ነበር። በትናንትናው እለት በታየው ከፍተኛ ህዝብ በተገኘበት ተቃውሞ ግን ሙስሊሙ የመንግስትን ዋነኛ የፕሮፓጋንዳ ማምረቻ ተቋም እየተቃወመ መምጣቱ፣ በመንግስት ላይ እምነት እያጣ መምጣቱን የሚያመላክት ነው።

በስፍራው የተገኘው ዘጋቢያችን እንዳለው የትናንትናውን ተቃውሞ ከዚህ በፊት ከተካሄዱት ሁሉ የተለየ የሚያደርገው የተቃውሞው ኢላማ የመጅሊስ አመራሮች መሆናቸው ቀርቶ መንግስት እየሆነ መምጣቱን ማሳየቱ ነው።

በትናንት ተቃውሞ ላይ የተገኙ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ተወካዮች መንግስት በማይወክሉን የመጅሊስ አባላትና የኡላማዎች ምክር ቤት አማካኝነት ምርጫውን በቀበሌ ለማድርግ በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረው፣ ምርጫው የሀይማኖት እንጅ የወረዳ ምክር ቤት ምርጫ ባለመሆኑ ተቀባይነት አይኖረውም ብለዋል።

የሙስሊሙ ተወካዮች ምርጫውን ሙስሊሙ በመረጣቸው አስመራጮች አማካኝነት በየመስኪዱ በተወሰነለት ጊዜ እንደሚያካሂዱ ይፋ አድርገዋል። ይህን በማድረጋቸው መንግስት በኮሚቴው አባላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ቢፈልግ በጸጋ ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። ተወካዮቹ  የመንግስት ሰዎች ስጋችንን ሊያስሩና ሊገድሉ ይችላሉ ነገር ግን ነፍሳችንና መንፈሳችን ሁልጊዜም ከእኛና ከፈጣሪያችን ጋር በመሆኑዋ ሊያስሩዋት አይችሉም ብለዋል።

ከ10 ቀናት በሁዋላ በሚገባው የረመዳን ጾም ሙስሊሙ ተቃውሞውን አጠንክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የመንግስት ደህንነቶች በኮሚቴ አባላት ላይ የሚያደርጉትን ማዋከብ መእመናኑ በጽኑ አውግዘዋል።

ሙስሊሙ ማህበረሰብ መንግስት በሀይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ እንዳይገባ፣  አህባሽን ለማስፋፋት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም፣ ህዝቡ አመራሩን በመስኪዱ በራሱ መንገድ እንዲመርጥ የሚሉ ጥያቄዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል።

መንግስት በበኩሉ ጥያቄውን የሚያቀርቡት ጥቂት አክራሪዎች ናቸው በማለት ጥያቄውን ለላመቀበል ያንገራግራል።

መንግስት እሱ የሚፈልጋቸውን ኮሚቴዎች ካስመረጠ ፣ ሙስሊሙም እራሱ የሚፈልጋቸውን ኮሚቴዎች ከመረጠ፣ በሁለቱ አመራሮች መካከል ውዝግብ ሊፈጠር እንደሚችል ይገመታል። መንግስት እየተከተለ ያለው ስትራቴጂም በዚህ መንገድ ሙስሊሙን ከሁለት መክፈልና እርስ በርሱ እንዲሻኮት በማድረግ ማዳከም ነው በማለት ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ አንድ ምሁር ያስረዳሉ።

የመጅሊስ አመራሮች ለአውልያው ጥያቄ እጅ ካልሰጡ፣ ወይም የአወልያ ተወካዮች ለመጅሊስ አመራሮች እጅ ካልሰጡ ውዝግቡ እንደሚቀጥል የሚናገሩት ምሁሩ፣ የመጅሊስ አመራሮች ምእመኑ ከእነርሱ ጋር አለመሆኑን እያወቁ እንኳን ከመንግስት የሚደርስባቸውን ጫና በመፍራት ከአወልያ ተቃዋሚዎች ጋር አብረው ለመስራት ፍላጎቱ እንኳ ቢኖር ድፍረቱ አይኖርም በማለት ያስረዳሉ።

እንደ እርሳቸው ገለጣ የኮሚቴው አባላት ለመጅሊስ አመራሮች የደህንነት ዋስትና በመስጠት ወደ እነሱ ካምፕ እንዲመጡ በማግባባት፣ መንግስት የሙስሊሙን ጥያቄ ለማዳከም የሚጠቀምበትን ካርድ እንዲጥል ማድረግ ነው።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide