ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አዲስ አበባ የሁሉም ናት ሲሉ ገለጹ

 (ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 2011/2011) ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ አዲስ አበባ የሁሉም ሆና እያለ የአንዱ ብቻ ናት መባሉ ትክክል አይደለም ሲሉ ገለጹ  ።

አንደኛ ዓመት የስልጣን ጊዜያቸውን መነሻ በማድረግ በወቅታዊው የሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ዶክተር አብይ እንደገለጹት በህገመንግስቱ የተቀመጠው የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ያላት የልዩ ጥቅም መብት ግን ሊረጋገጥ ይገባል።

ይህንን ሀሳብ ደግሞ ኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሰው ሊደግፈው ይገባል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በህግ የበላይነት፥ ስለክልሎች እና በሀገሪቱ ስለተከሰቱ ግጭቶች እንዲሁም በመፈናቀል ጉዳዮች ላይም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢሕአዴግ አለ ወይ? ስለሚባለው ጉዳይ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ግንባሩ የቀድሞ ጥምረቱ እንዳለና እሁንም ሀገሪቱን እየመራ ያለው ይሄው ጥምረት መሆኑን ገልጸዋል።

ብዙዎች የተለያየን የሚመስላቸው የልዩነት ሀሳቦች ስላሉ ነውም ብለዋል። ይሕም አራቱ ፓርቲዎች በውስጣዊ ውይይት ብቻ ይገድቡት የነበረው ሂደት ቀርቶ ፓርቲዎቹ የልዩነት አቋማቸውን በአደባባይ መግለፃቸው እንደሆነ ነው የገለጹት ። ይህ አካሄድ ወደፊትም ይቀጥላል ሆኖም ተግባራዊ የሚሆነው በጋራ የወሰነው ሀሳብ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

አዲስ አበባ የሁሉም ሆና እያለ  የአንዱ ብቻ ናት መባሉ ትክክል አይደለም ሲሉም በመዲናዋ ጉዳይ ላይ ያለውን ንትርክም መልክ ለማስያዝ ሞክረዋል ።ይሕን ሲሉ ግን በህገመንግስቱ የተቀመጠው የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ያላት የልዩ ጥቅም መብት ግን ሊረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት።

በኮዬ ፌጬ የኮንደሚኒዮም ግንባታ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል ወሰን ያለው ውዝግብ ተፈቶ ለኮንዶሚኒዮም ባለእድለኞች ቤቶቹ እንዲተላለፉ እየተሰራ ነው።

የፌደራል መንግስት ተዳክሟል ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ደግሞ መለኪያው መሆን ያለበት ሀገር ስትወረር መመከት ሲያቅተው ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችን በብቃት መመከት አልችል ሲል ሊሆን ይገባል ብለዋል።

አሁን ግን በዚህ መልኩ የሚገለፅ አንዳችም ተግዳሮት አልገጠመንም በክልሎች የሚፈጠሩ ችግሮች ላይ ጣልቃ የማንገባው ክልሎች በራሳቸው መፍታት አለባቸው ብለን ስለምናምን ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በኦዲፒና በአዴፓ እንዲሁም በኦዲፒ በራሱ ውስጥ አንድነት እንጂ ምንም አይነት የተለየ ልዮነቶች የለም ፥ ነግር ግን በመካከላቸው የልዮነት ሀሳብ ይኖራሉ። እነሱንም በመነጋገር እየፈታን ሲሉም ነው የገለጹት ።

እንደ ዶክተር አብይ ገለጻ የአማራና የትግራይ ክልል ውጥረት በቀጣይ በእርግጠኝነት የሚረግብና ወደ ሰላም የሚመለስ ነው፡፡ እናም ሁሉቱም ወገኖች በኦሮሚያና በሶማሊያ ክልሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ያመጣውን ኪሳራ ስለሚያውቁ በመካከላቸው ያለውን ልዮነት በሰላም ይፈታሉ ነው ያሉት፡፡ የትግራይና የአማራ ሕዝብ የፀብ ፍላጎት እንደሌላቸውም ነው ያብራሩት፡፡

በግጭት ጥያቄን በዘላቂነት መፍታት አይቻልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጉዳዩ በሕግ አግባብ መፍትሔ እንደሚያገኝም ጠቅላይ ሚንስትሩ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለቻ አብራርተዋል፡፡