ቦይንግ ኩባንያ በ737 ማክስ አውሮፕላን ላይ የነበረውን “ኤምካስ” የተሰኘው መቆጣጠሪያ መቀየሩን ገለጸ

 (ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 19/2011) በአሜሪካ የሚገኘው አውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ኩባንያ በ737 ማክስ አውሮፕላን ላይ የነበረውን “ኤምካስ” የተሰኘው የመቆጣጠሪያ ሲስተም በመቀየር ችግሩን ፈትቼዋለሁ ሲል ገለጸ።

እጅግ ዘመናዊ ከሚባሉት የቦይንግ 737 ማክስ ስሪቶች በኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ ተከስክሰው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ካለቁ በኋላ ቦይንግ ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል ።

ይሕም ሆኖ ግን እንዳይበሩ የተደረጉት የቦይንግ የማክስ ስሪቶች በቅርቡ ወደ ሥራ ለመመለስ እስካሁን የወሰነ ሀገር የለም ።

የኢንዶኒዥያው ላየን አየር መንገድ አውሮፕላን በተከሰከሰ በአምስተኛ ወሩ የኢትዯጵያ አየር መንገዱ አደጋ ሲደገም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ አየር መንገዶች የ737 ማክስ ስሪቶችን ላለማብረር ወስንዋል። ይህም በቦይንግ ላይ የቢሊዮን ዶላሮች ኪሳራን ማድረሱ ነው የተገለጸው።

እናም ቦይንግ ኩባንያ ዋናው የችግሩ ምንጭ እንደሆነ የሚጠረጠረውን “ኤምካስ” የተሰኘውን የመቆጣጠሪያ ሲስተም ቀይሬያለሁ ብሏል ።

ያም ሆኖ እንዳይበሩ የተደረጉት የብዙ ሃገራት የማክስ ስሪቶች በቅርቡ ወደ ሥራ ለመመለስ እስካሁን አልወሰኑም ።

ይህም የሆነው ቢያንስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተከሰከሰበትን ምክንያት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ የምርመራ ውጤት ስለሚጠበቅ ነው ተብሏል።

ኤምካስ የተባለውን ሲስተም አድሻለሁ የሚለው ቦይንግ አሁን አውሮፕላኖቹ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ቢገቡ ማስጠንቀቂያ የሚልክ ዘዴኝ የያዘ ነው። ይህ ዘዴ ቀደም ሲል እንደ አማራጭ የነበረ እንጂ አስገዳጅና መደበኛ ሲስተም ሆኖ ከቦይንግ የቀረበበት ሁኔታ ጨርሶ እንዳልነበረ የአቪየሽን ባለሞያዎች ይናገራሉ።

ይህ አሁን ተሻሽሎ ይገጠማል የሚባለው የቅድመ ጥንቃቄ ሰጪ ሲስተም በኢንዶኒዢያውም ኾነ በኢትዯጵያው አየር መንገድ ላይ ያልነበረ ነው ተብሏል። ቦይንግ እንደገለጸው ይህ ሲስተም መገጠሙ አውሮፕላኑ የሚቃረኑ ምልክቶችን ሲሰጥ ለፓይለቶቹ ጥቆማን ይሰጣል።

ቦይንግ ለደንበኞቹ ይህን ሲስተም የምገጥምላችሁ በነጻ ነው፤ አንዳችም ክፍያ አልጠይቃችሁም ብሏል።

ቀደም ሲል የነበረው ሴንሰር ግን የኢንዶኒዢያው  አውሮፕላን ምርመራ ውጤት እንዳመላከተው  አውሮፕላኑ በአፍጢሙ እንዲደፋ የሚያደርግበት ሁኔታ አለ። ይህም የሚሆነው ሚዛኑን ለመጠበቅ የሚልከው መልዕክት (ሲግናል) እርስበርሱ የሚጣረስ እንደሆነ ነው የተገለጸው።

ይህም ከአብራሪዎቹ ቁጥጥር ውጭ የሚሆን ነገር ነው ተብሏል። የተከሰከሰው የኢንዶኔዢያ አየር መንገድ ከ20 ጊዜ በላይ የአውሮፕላኑ አፍንጫ ቁልቁል እንዲያዘምና እንዲምዘገዘግ አድርጎታል ።

አሁን ቦይንግ አድሼዋለሁ የሚለው ሶፍትዌር በአውሮፕላኑ አፍንጫ የምትገኘው ሴንሰር እርስ በርሱ የሚጣረስ መልዕክት ካስተላለፈ ኤምካስ የተሰኘውን መቆጣጠሪያ ልክ እንደ ኤሌክትሪክ ባልቦላ ራሱን በራሱ እንዲያጠፋ የሚያደርግ ነው ተብሏል።