(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 8/2010)
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን መልቀቂያ ማቅረባቸውን ገለጹ።
አቶ ሃይለማርያም በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ቀርበው ስልጣን ለመልቀቅ የወሰኑት ለሃገር መረጋጋትና ለሰላማዊ የስልጣን ሽግግር መሆኑን ገልጸዋል።
ጥያቄያቸው አባልና ሊቀመንበር በሆኑበት ድርጅት በደኢህዴንና በኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ተቀባይነት አግኝቷልም ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልቀቂያ ተግባራዊ የሚሆነው ግን በኢሕአዴግ ምክር ቤትና በፓርላማው ሲጸድቅ ይሆናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በመግለጫቸው እንዳሉት ኢትዮጵያ በአስከፊ ሁኔታ ላይ ትገኛለች።
እናም ለሀገር መረጋጋትና ለሰላም ስል ስልጣኔን በሰላም ለቅቄያለሁ ሲሉ በቀጥታ በተላለፈው የቴሌቪዥን ስርጭት አስታውቀዋል
ኢሕአዴግ ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር እስኪመርጥና ጥያቄው በፓርላማ እስኪጸድቅም በስራቸው ላይ እንደሚቆዩ አቶ ሃይለማርያም ተናግረዋል።
አቶ ሃይለማርያም እንዳሉት ከስልጣን ለመነሳት ያቀረቡት ጥያቄ በድርጅታቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ደኢሕዴን/እና በኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ተቀባይነት አግኝቷል።
አቶ ሃይለማርያም ይህን ይበሉ እንጂ የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ መቼ ስብሰባ እንዳካሄደ የገለጹት ነገር የለም።
በኢትዮጵያ አስከፊ ሁኔታ ተከስቷል፣አሁን ለተፈጠረው ችግርም የመፍትሄው አካል እሆናለሁ ያሉት አቶ ሃይለማርያም ሕዝቡም በመፍትሄ ማምጣቱ በኩል ተግባራዊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የፌደራል መንግስት ስልጣን ከመያዛቸው በፊት የደቡብ ክልል ፕሬዝዳንት ነበሩ።
በኋላ ግን በሲዳማ ብሄር ተወላጆች በተነሳባቸው ተቃውሞና በሃዋሳ በተካሄደው ጭፍጨፋ ተጠያቂ ሲደረጉ አቶ መለስ ዜናዊ አማካሪ አድርገው ወደ ፌደራል መንግስት ወስደዋቸዋል።
በ2002 የኢሕአዴግ ምክትል ሊቀመንበር በመሆንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ።
በ2004 አቶ መለስ ዜናዊ ሲሞቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብለው በአቶ በረከት ስምኦን አማካኝነትም ለ3 ቀናት ተሰይመው ነበር።
በኋላ ግን ከሕወሃት በኩል ሕጉን ያልጠበቀ ሹመት ነው ተብለው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ከቆዩ በኋላ ፓርላማው ከእረፍት ተጠርቶ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን እንዲሾሙ ተደርጓል።
በ2ኛው የስልጣን ዘመንም በ2007 በተካሄደው ምርጫ ኢሕአዴግ መቶ በመቶ በሆነ ድምጽ አሸንፌያለሁ ባለ ጊዜ በድጋሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ተደርገው ተሹመው ነበር።
አሁን ደግሞ የስራ ዘመናቸውን ሳይጨርሱ በሕዝብ ግፊት ስልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበዋል።