ጳግሜ ፬(አራት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጠ/ሚኒስትሩ ትላንትና እና ዛሬ ለሕትመት በበቃው ከመንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ እንደተናገሩት “የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በርግጥም ለኢትዮጽያ ሕዝብ ዴሞክራሲ፣መልካም አስተዳደር ልማትና ሠላምን ለማምጣት አጀንዳ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ከሆነ አክራሪነትንና ሽብርተኝነትን ከመንግስት ጎን ተሰልፈው ሊያወግዙ ይገባል ብለዋል፡፡
” በኢትዮጽያ አክራሪነትና ሽብርተኝነት የለም ብለው የሚያስቡ ከሆነ እነዚህ ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የሉም ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በዓለም ላይ እየተካሄደ ያለውን አያውቁም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ስራና ሕዝቡን ለመምራት የሚያስችል ትልቅ ኃላፊነትና ብቃቱ የላቸውም ማለት ነው፡፡ ብቃቱ አለን ብለው የሚያስቡ ከሆነ ዓለማዊውንና አገራዊ ሁኔታ በአግባቡ ገምግመው ሸብርተኛነትን እንደዚሁም አክራሪነትንና ጽንፈኝነትን በኢትዮጽያ እያቆጠቆጠ የመጣና ሕዝቡን በግላጭ እየጎዳ ያለ እንደሆነ ማንም
የሚያውቀውን እየካዱ የሚሄዱ ከሆነ እነዚህ ሰዎች ዓላማቸው ሰላማዊ፣ሕጋዊና ለአገሪቱ የሚጠቅም የፖለቲካ ስርዓት
ውስጥ ተወዳድረው ለማሸነፍ የተዘጋጁ ኃይሎች አይደሉም ማለት ነው” ብለዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሁንም ቢሆን ከድርጊታቸው ታቅበው በሰላማዊ፣ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ተወዳድረው ማሸነፍ እንዳለባቸው የመከሩት አቶ ኃ/ማርያም ፣ ተወዳድረው ማሸነፍ ሲያቅታቸው ከእኔ የቀረ እንደሆነ አገሩቱዋ ትቀጣጠል
ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገቡ ከሆነ አጥፊዎች ናቸው ማለት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አቶ ኃ/ማርያም ባለፈው ሳምንት እሁድ በተካሄደውና በመንግስት በሚደገፈው የአደባባይ ሰልፍ ከ600ሺ በላይ ሕዝብ
መውጣቱን አስታውሰው ይህ አክራሪ ኃይሎች ከሕዝቡ መነጠላቸውን ያሳያል ብለዋል፡፡ አክራሪና ጽንፈኛ ኃይሎች ከሕዝቡ ከተነጠሉ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ቀላል ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት እሁድ በአዲስአበባ በመስቀል አደባባይ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠርተውታል የተባለው ሰልፍ በቀጥታ በመንግስት የተመራ ሲሆን የቀበሌ ሹማምንት በየቤቱ እየሄዱ ነዋሪዎች በሰልፉ ላይ እንዲገኙ የግዳጅ ፊርማ ሲያስፈርሙ እንደነበር መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡