ታህሳስ 21 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የማላዊን ድንበር ሲያቋርጡ ከተያዙት ኢትዮጵያውያን መካከል አራቱ ረዥም ጊዜ በዘለቀ ረሀብ ሞተው አስከሬናቸው በሀይቅ ውስጥ ሲገኝ፤ ቀሪዎቹ 90 ኢትዮጵያውያንም በፍርድ ቤት ጥፋተኞች ተባሉ
አሶሼትድ ፕሬስ የግብፅን አየር መንገድ ባስልጣናት ጠቅሶ ከካይሮ እንደዘገበው፤ ኢትዮጵያውያኑ በሱዳን ድንበር በኩል ወደ ግብፅ ገብተው የሲና በረሃን በማቋረጥ ወደ እስራኤል በሕገ ወጥ መንገድ ለመግባት ሲሞክሩ ነበር፤ በአየር መንገዱ ሰራተኞች አማካይነት በቁጥጥር ስር የዋሉት።
ኢትዮጵያውያኑ በእስራኤል ሀገር ስራ ለመፈለግ በማሰብ ረጅም እና አስቸጋሪ ጉዞዎችን ተጉዘው ግብፅ መድረሳቸውን የገለፁት ባለስልጣናቱ፣ ባለፈው ቅዳሜ 51ዱ፤ በማግስቱ ደግሞ 42ቱ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል ብለዋል።
ከ2006 (እ.ኤ.አ) ወዲህ ብቻ ወደ 50 ሺህ የሚጠጉ አፍሪካውያን የሲና በረሃን አቋርጠው የ250 ኪሎ ሜትር ርቀት ባለው የግብፅ ድንበር በኩል በሕገወጥ መንገድ ወደ እስራኤል ገብተዋል ብሏል- ዘገባው።
በተያያዘ ዜና የማላዊ ፍርድ ቤት በ90 ኢትዮጵያውያን ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፏል።
ኢትዮጵያኑ ማላዊ ሀይቅን አቋርጠው ወደ ማላዊ ከገቡ በኋላ ከፖሊስ ለማምለጥ ከተሸሸጉበት ማላዊ ሐይቅ ላይ ነው ሊያዙ የቻሉት።
የናካታ ቤይ ፖሊስ ቃል አቀባይ ሰርጂያንት ማርቲን ከዋናሊ እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያውያኑ በሕገወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው ወደ ማላዊ በመግባት ተከሰው ጥፋተኛ ናቸው ተብለዋል።
ኢትዮጵያውያኑ በፖሊስ እንደሚፈልጉ ከማላውያን የጀልባ ሰራተኞች በመስማታቸው ለአራት ቀናት ያህል በሐይቁ ላይ ለመቆየት ተገደው እንደነበረ የገለፁት ቃል አቀባዩ፣ በዚህ ቆይታቸው ወቅትም ስምንቱ ኢትዮጵያውያን በጀልባ ሐይቁ ላይ እንዳሉ በረሃብ ምክንያት ህይወታቸው በማለፉ እስከሬናቸው በሐይቁ ውስጥ መገኘቱን ገልፀዋል።
ጥፋተኛነታቸው የተረጋገጠባቸው 90 ኢትዮጵያውያን ከ20 እስከ 40 ዓመት በሚደርስ የ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ዞዲያክ የተባለው የማላቂ የዜና አውታር ገልጿል።