ግንቦት ፳፮(ሃያ ስድስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- “መና” የተባለው የግብጽ ዜና አገልግሎት እና “አል አህራምስ” የተባለው የአረብኛ ድረ ገጽ እንደገዘቡት፤ ወደ ሀገራቸው “ዲፖርት” የተደረጉት ኢትዮጰያውያን በህገ ወጥ መንገድ ወደ ግብጽ በመግባት ወደ እስራኤል ለመሻገር ሲሞክሩ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ ናቸው።
ተመላሾቹ ኢትዮጰያውያን ግብጽ ከሱዳን ጋር በምትዋሰንበት ደቡባዊ ድንበር በኩል አድርገው ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ አስዋን ሲገቡ በፖሊስ ተይዘው መታሰራቸውን የዘገቡት የዜና ተቋማቱ፤ ላለፉት ሁለት ሳምንታተ በእስር ከቆዩ በሁዋላ ካይሮ ከሚገኘው ከኢትዮጰያ ኤምባሲ ጋር በመነጋገር ወደ ሀገራቸው እንዲሸኙ መደረጋቸውን አመልክተዋል።
በአውሮፕላን ማረፊያ የነበሩ የደህንነት ምንጮች ለ”መና” እንደነገሩት፤ ከተጠረዙት ኢትዮጵያውያን መካከል ሶስቱ ህጻናት ናቸው።
በፖሊስ ምርመራ እንደተመለከተው ኢትዮጰያውያኑ እቅዳቸው በሲናይ በረሀ በማቆራረጥ እና ምስራቃዊውን የሀገሪቱን ድንበር በመሻገር ወደ እስራዔል በመግባት ስራ ለመስራት ነበር።
በግብጽና በኢትዮጰያ መካከል ያለው ግንኙነት – ኢትዮጰያ በዓባይ ላይ ግድብ ለመስራት ከጀመረች በሁዋላ እየተበላሸ መምጣቱን የሚዲያ ተቋዋማቱ ጠቅሰዋል።
በሲናይ በረሀ አቆራርጠው ወደ እስራኤል በመሄድ ስራ መስራት የሚፈልጉ አፍሪካውያን በተደጋጋሚ በግብጽ ፖሊሲች መያዛቸውን “መና” አውስቶአል።
ኢትዮጵያ በቅርቡ አንድ የግብጽ ጋዜጠኛ ከአገሪቱ እንዲወጣ ማድረጓ ይታወቃል።