በምዕራብ ኦሮምያ ዞን የፌደራል ፖሊሶች ከህዝብ ጋር መጋጨታቸው ተሰማ

ግንቦት ፳፮(ሃያ ስድስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፈው ቅዳሜ አቡና  በሚባል ወረዳ የፌደራል ፖሊሶች ነዋሪዎችን መደብደባቸውንና ቁጥራቸው ያልታወቁትንም ይዘው ማሰራቸውን የአካባቢዎች ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።

የግጭቱ መነሻ በቅርቡ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በወረዳው የተነሳውን ተቃውሞ አስተባብሮአል የተባለው መንጌ ጉደታ እንዲፈታ ህዝቡ ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ ነው።

ወጣቱ እግሩ በድብደባ ብዛት መሰበሩን የሚገልጹት አካባቢው ነዋሪዎች፣ ነዋሪዎች ወጣቱ ካልተለቀቀ ፖሊስ ጣቢያውን እናቃጥላለን ማለታቸውን ተከትሎ በአካባቢው የተሰማራው የፌደራል ፖሊስ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ድብደባ ፈጽሟል።

ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ወጣቶችም ተይዘው ታስረዋል።

ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ የፌደራል ፖሊስ በአካባቢው መሰማራቱንና ውጥረቱ እንዳለ መሆኑን ነዋሪዎች አክለው ገልጸዋል።