(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 22/2011) በግብጽ በሳምንቱ መጨረሻ በአንድ የቱሪስት አውቶቡስ ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ግብጽ በአሸባሪዎች ላይ ጥቃት መክፈቷን ገለጸች።
በዚህም ጥቃት 40 ያህል መገደላቸውንም ይፋ አድርጋለች።
ባለፈው አርብ ጊዛ በተባለው የግብጽ የቱሪስት መናሃሪያ በመንገድ ላይ የተጠመደ ፈንጂ ፈንድቶ በአንድ የቱሪስቶች መጓጓዣ ላይ ባደረሰው ጉዳት ሶስት የቬትናም ዜጎች ተገድለዋል።
እንዲሁም አንድ ግብጻዊ አስጎብኚም በተመሳሳይ ሕይወቱ አልፏል።
ለዚህ ጥቃት ሃላፊነቱን የወሰደ ወገን ባይኖርም ግብጽ እስራኤላዊ አሸባሪዎች በድርጊቱ እጃቸው አለበት በማለት ጥቃት ከፍታለች።
አሸባሪዎቹ በሌሎች የቱሪስት ማዕከላት እንዲሁም በቤተ ክርስቲያኖችና በወታደራዊ ተቋማት ላይ ተከታታይ ጥቃት ለመፈጸም አቅደዋል ያለችው ግብጽ ጥቃቱ በተፈጸመበት ስፍራ በወሰደችው የአጸፋ ርምጃ 30 አሸባሪዎችን መግደሏን ገልጻለች።
ቀሪዎቹ አስሩ ደግሞ የተገደሉት ኤል አሪሽ በተባለው ስፍራ መሆኑም ተመልክቷል።
ግብጽ በጀመረችው አሰሳና የአጸፋ ምላሽ የጦር መሳሪያዎችና የቦምብ ማቀነባበሪያ ማሽኖችን ጭምር በቁጥጥር ስር ማዋሏንም አስታውቃለች።
ጎብኚዎች በከፍተኛ ቁጥር የሚገቡበት እንዲሁም በቁጥር አናሳ የሆኑት የግብጽ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች የገናን በአል የፊታችን ታህሳስ 29 በሚያከብሩበት ወቅት ችግር እንዳይከሰት ጥበቃው መጠናከሩም ተመልክቷል።