በአርሲ ነጌሌ ከ30 በላይ ሱቆች ታሸጉ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 23/2011) በአርሲ ነጌሌ ከ30 በላይ ሱቆች እንዲታሸጉ የከተማው አስተዳደር ውሳኔ አስተላለፈ።

ባለሱቆቹ ህጋዊ መሆናቸውን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ቢያቀርቡም የከተማው አስተዳደር ሱቆቹ ለሌሎች የሚሰጥ በመሆኑ በአስቸኳይ ለቃችሁ ውጡ ተብለዋል።

ላለፉት ስድስት ወራት በከተማው አስተዳደርና በወጣቶች ከፍተኛ ጫና ሲደረግባቸው የነበሩት ባለሱቆቹ ለ20 ዓመታት በህጋዊነት ሲሰሩባቸው የነበሩት ሱቆች ከእሁድ ጀምሮ ታሽገውባቸዋል።

የከተማዋ ሌሎች ነጋዴዎችም በማንነታችን የተነሳ የከተማው አስተዳደር የሚያደርግብን ጫና በመጨመሩ ከተማዋን ለቀው ለመሄድ በዝግጅት ላይ እንዳሉም ገልጸዋል።

የከተማው አስተዳደር ምላሽ እንዲሰጠን ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም።

በተለመዶ አሮጌው መናሃሪያ በሚባለው አካባቢ ነው።

የዛሬ 20 ዓመት ገደማ የአርሲ ነጌሌ ከተማ አስተዳደር ከ30 በላይ አነስተኛ ሱቆችን በመስራት ለነጋዴዎች ቁልፍ ሸጦ ያስረክባቸዋል።

ኢሳት ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት አንድ ባለሱቅ እንደሚሉት ያን ጊዜ ማንነታችን ተጠይቆ፣ ብሔራችን መስፈርት ሆኖ የተሰጠን አልነበረም።

አቅሙ ያለውና የተጫረተ ነጋዴ ቁልፍ ገዝቶ መነገድ ጀምሯል።

ለ20 ዓመታት በህጋዊነት ግብር እየከፈሉበት ሲኖሩ ቆይተዋል። ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ግን ሁኔታዎች ጥሩ አይደሉም ነው የሚሉት።

በተለይ የቄሮ የመብት ትግል ከተቀጣጠለበት ጊዜ አንስቶ ማንነት ላይ ያተኮረ ትንኮሳና ጥቃት የከተማው ነጋዴዎች ላይ በከፍተኛ ደረጃ ይደረጋል ነው የሚሉት።

በመናሃሪያ አካባቢ እያንዳንዱን ሱቅ በ8500 ብር ቁልፍ ገዝተው ስራ የጀመሩትና ለ20 ዓመታት ቤተሰብ መስርተው ልጆቻቸውን የሚያሳድጉበትን ስራ እየሰሩ እንደነበሩ የሚገልጹት ነጋዴዎች ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ ሱቆቹን አስረክበን እንድለቅ በከተማው አስተዳደር ጫና እየተደረገብን ነው ይላሉ።

ህጋዊነታችንን የሚያሳይ፣ ግብር የከፈልንበትንም ሆነ ሌሎች ማስረጃዎች ብናቀርብ የከተማው አስተዳደር ሱቆቹ ለሌላ ጉዳይ ስለተፈለጉ የግድ መልቀቅ አለባችሁ የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸውም ይገልጻሉ።

ከከተማው አስተዳደር ጋር የነበራቸው ህጋዊ ስምምነት የሱቅ ኪራይና ግብር መክፈል፡ እንዲሁም በየአምስት ዓመቱ ኮንትራት ማሳደስ የሚል እንደሆነ የሚገልጹት ነጋዴዎቹ ምንም ህጋዊ ምክንያት በሌለው መልኩ ጫና መፍጠሩ ተገቢ አይደለም ይላሉ።

ህዝባዊ እምቢተኝነቱ በሚካሄድበት ወቅት ነጋዴዎቹ በስጋት ላይ እንደነበሩና ለቀው እንዲወጡ ማስፈራሪያ ይድርስባቸው እንደነበርም ለኢሳት ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው እንግዲህ የከተማው አስተዳደር ባለፈው ዕሁድ ሱቆቹን በሙሉ ያሸገባቸው።

ነጋዴዎቹ ከከተማው አስተዳደር ጫናው ሲበረታባቸው እስከ ክልል ድረስ ሄደው አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን ጉዳዩ የሚመለከተው የክልል ባለስልጣን አዲስ ህግ እስካልወጣ ድረስ ሊነኩ አይገባም የሚል ትዕዛዝ ለከተማው አስተዳደር ማስተላለፉን ይገልጻሉ።

የከተማው አስተዳደር ግን የበላይን ትዕዛዝ በመግፋት ሱቆቹን ማሸጋቸውን ነው ነጋዴዎቹ የሚገልጹት።

በከተማዋ ማንነትን መሰረት ባደረገ ጥቃት ነጋዴዎች ላይ የተለያዩ በደሎች እንደሚደርሱም ኢሳት ያነጋገራቸው ነጋዴዎች ገልጸዋል።

ነጋዴዎቹ ቅሬታቸውን ለማሰማት ወደ ከተማው አስተዳደር ሔደው ሲያነጋግሩም “አማራጭ የላችሁም፤ዕቃችሁን ይዛችሁ ውጡ” የሚል ምላሽ ተሰጥቶናል ብለዋል።

ግብር ከፋይ መሆናቸውን፣ የቫት ተጠቃሚ እንደሆኑም የሚናገሩት ነጋዴዎቹ መፍትሄ የሚሰጣቸው አካል አላገኘንም ይላሉ።

በአዲሱ መናኸሪያ ዙሪያና በገበያ ውስጥ በርካታ የማዘጋጃ ቤት ሱቆችም እንዲለቁ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደተሰጣቸውም ታውቋል።

ጉዳዩን በተመለከተ ማብራሪያ ለማግኘት ወደ አርሲ ነጌሌ ከተማ አስተዳዳር ስልክ ብንደውልም ለጊዜው አልተሳካልንም።