ጋዜጠኞች ፍርድ ቤት ቀረቡ

ሚያዚያ ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የመሐል ዳኛ እንዳሻው አዳነ፣ ቀኝ ዳኛ ሙሉጌታ ኪዳኔ እና በቅርቡ በዳኛ አራጋው በሪሁን የተተኩት የግራ ዳኛ ሁሴን ይመር ባስቻሉት ችሎት ላይ የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የቆሙበትን ችሎት ለመታዘብ የመጡ በርካታ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛ ጋዜጠኞች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ተወካዮች እና የፍትህ ጋዜጣ አንባቢያን የተገኙ ሲሆን የችሎቱ አዳራሽ በርካታ ሰው ከሚያስተናግደው 15 ወንጀል ችሎት ወደ ጠባቡ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት በመውሰዱ ብዙሃን የፍርድ ቤቱን ችሎት ሊከታተሉ የመጡ ታዛቢዎች ከውጭ ለመቆም ተገደዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ችሎቱ ለዛሬ የተቀጠረው አቃቤ ህግ ባቀረበው አቤቱታ እና የፍትህና የነጋድራስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጆች በጽሑፍ የሰጡትን መልስ አገናዝቦ ውሳኔ ለመስጠት መሆኑን አውስቶ፣ ነገር ግን አቃቤ ህግ ሃሙስ ሚያዚያ 11 ቀን 2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት ላይ ዓርብ ሚያዚያ አምስት ቀን 2004 ዓም በወጣውን ፍትህ ጋዜጣ ላይ በገጽ 4 ላይ በክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) የተጻፈው ማቆሚያና ገደብ ያጣው የሚስኪኗ እናቴ እንባ! የሚለው ጽሑፍ ላይ የፍርድ ቤት ነፃነትን የሚጋፋ ጽሑፍ ተስተናግዷል በሚል ተጨማሪ አቤቱታ ማቅረቡንና ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝም በሬጄስትራር በኩል ሦስት ገጽ የድጋሚውን የዐቃቤ ህግ አቤቱታ ምላሽ መስጠቱን አውስቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለመስጠት በመጀመሪያ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) ጽሑፉን በእርግጥ እርሳቸው ስለመጻፋቸው በቀጣይ ቀጠሮ ከማረሚያ ቤት ወደ ፍርድ ቤቱ ችሎት ቀርበው እንዲያስረዱ ውሳኔ ማስተላለፉን ጠቅሶ ተለዋጭ ቀጠሮ ለዓርብ ጠዋት ሚያዚያ 19 ቀን 2004 ዓ.ም ተለዋጭ ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱ ተበትኗል፡፡

በፍርድ ቤት አካባቢ ብዙ ወጣቶች የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅን የችሎት ውሎ ለመከታተል በፍርድ ቤት በመታየታቸው የደህንነት ሠራተኞች የፍትህ ጋዜጠኞችን በተለይም ዋና አዘጋጁን በቅርብ እርቀት መከታተል ጀምረዋል፡፡

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide