ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና ታዋቂው ፖለቲከኛ አንዱአለም አራጌ ላይፈቱ ይችላሉ ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 2/2010)

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና ታዋቂው ፖለቲከኛ አንዱአለም አራጌ የይቅርታ ሰነድ አንፈርምም በማለታቸው ከእርስ ላይለቀቁ ይችላሉ ተባለ።

 

ሁለቱም እስረኞች የአርበኞች ግንበት 7 አባል ነን ብላችሁ ፈርሙ ተብለው በሌለንበት ነገር አንፈርምም፣ያጠፋነውም ነገር ስለሌለ ይቅርታ አንጠይቅም ብለዋል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደገለጹት በእስርቤቱ ሃላፊዎችና በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንዲሁም በታዋቂው ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌ መካከል አለመግባባት ተፈጥሯል።

ችግሩ ደግሞ ሁለቱም እስረኞች ይቅርታ እንዲጠይቁና የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባል ነበርን ብለው እንዲፈርሙ በመጠየቃቸው ነው።

እንደ ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ ገለጻ መሰረት ቢሆን ኖሮ እስክንድር ነጋና አንዱለም አራጌን ጨምሮ ከ 700 በላይ እስረኞች በይቅርታና ክሳቸው ተቋርጦ መፈታት ነበረባቸው።

በትላንቱ የአቃቤ ህግ መግለጫ የነ እስክንድር ጉዳይ በይቅርታ ቦርድ ታይቶ ወደ ፕሬዝዳንቱ ለውሳኔ ከቀረበ በኋላ እስረኞቹ እንደሚለቀቁ ተነግሮ ነበር።

በኋላ ላይ ግን ሂደቱ ተገለባበጠና አስክንድርም ሆነ አንዷለም ይቅርታ እንዲጠይቁ እንዲሁም የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት ነን እንዲሉ የሚያስገድድ ሰነድ እንደቀረበላቸው ተነግሯል።

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋም ሆነ አንዷለም አራጌ ግን ወትሮም ቢሆን ይህ ጥያቄ ከዚህ ቀደም ቀርቦላቸው ምንም ጥፋት የለብንም፣ የቅርታም አንጠይቅም በማለታቸው ለእስር ተዳርገው እንደቆዩ ነው የሚታወቀው።

እናም አሁንም ለቀረበላቸው የይቅርታ ጠይቁ ጥያቄ ተመሳሳይ አቋም በመያዛቸው ከእስር የመለቀቃቸው ነገር አጠራጣሪ ሆኗል ተብሏል።

በጉዳዩ ላይ ከአገዛዙ እስካሁን የተሰጠ መግለጫ ባይኖርም ጋዜጠኛ እስክንድርና አቶ አንዷለም አራጌ በአቋማቸው ጽኑ በመሆናቸው ከእስር ይወጣሉ ተብሎ እንደማይጠበቅ የቅርብ ምንጮቻችን ገልጸዋል።