ወደ ባህር ከተጣሉ ኢትዮጵያውያን 25ቱ መጥፋታቸው ታወቀ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 2/2010)

ወደ ባህር ከተጣሉ ኢትዮጵያውያን 25ቱን ማግኘት እንዳልተቻለ የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ጽ/ቤት አስታወቀ።

በ4 ጀልባዎች ተጭነው ትላንት ወደ የመን እየተጓዙ ከነበሩትና በዋና እንዲሻገሩ ከተገደዱት ስደተኞች መካከል 25ቱ ኢትዮጵያውያን እስከዛሬ ድረስ ሊገኙ እንዳልቻሉ ጽ/ቤቱ ገልጿል።

በሌላ ዜና ሞዛምቢክ 50 ኢትዮጵያውያንን ማባረሯ ታውቋል።

ኢትዮጵያውያኑ በዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት ትብብር ወደ ኢትዮጵያ መላካቸው ተገልጿል።

600 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በ4ቱ ጀልባዎች ተሳፍረው ነበር ይላሉ መረጃዎቹ።

የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ጽሕፈት ቤት ቃልአቀባይ ጆኤል ሚሊማን።

ባልተለመደ ሁኔታ ብዙ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያዊን ስደተኞች ከሶማሊያ ተነስተው በየመን ሻብዋ ግዛት ከሚገኘው የባህር ጠረፍ ይቃርባሉ።

መሬት ከመርገጣቸው ቀደም ብሎ ግን ከጀልባው ወርደው ወደ ባህርዳርቻው በዋና እንዲደርሱ ከህገወጥ አዘዋዋሪዎቹ ግዴታ ይመጣባቸዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው ወደ ባህርዳርቻው ከመድረሳቸው በፊት በዋና እንዲሻገሩ ከተጣሉት መሃል 25 ኢትዮጵያውያን የገቡበት አይታወቅም።

እስከዛሬም ድረስ የአንዳቸውም አካል ሊገኝ እንዳልቻለ ታውቋል።

ጦርነት ወደሚያምሳት የመን በየአመቱ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ስደተኞች እንደሚገቡ የገለጸው አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይ ኦ ኤም በበኩሉ ከአፊርካ ቀንድ ብቻ 87ሺ ስደተኞች በ2017 የመን መድረሳቸውን አስታውቋል።

ባለፈው ወር ከ30 በላይ ስደተኞች በዚሁ የየመን የባህር ክልል ውስጥ ሰጥመው መሞታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ትላንት ወደ የመን ሊቃረቡ ሲሉ ወደ ባህር የተጣሉትን ስደተኞች በተመለከተ ሕወሃት ከሚመራው መንግስት የተባለ ምንም ነገር የለም።

ባለፉት 24 ሰአታት የተገኘ ሰው አለመኖሩን የሚገልጹት የስደተኛ ጉዳይ ሰራተኞች ምናልባትም ሳይሞቱ እንዳልቀሩ ስጋታቸውን ይናገራሉ።

በሌላ በኩል ሞዛምቢክ 50 ኢትዮጵያውያንን ከሃገሯ ማባረሯን አስታውቃለች።

የሞዛምቢክ የስደተኞች አገልግሎት ባሰራጨው መረጃ እንደተገለጸው 40 ኢትዮጵያውያን የተገኙት በሞዛምቢክ ጥቅጥቅ ደን ውስጥ ሲሆን 10ሩ ደግሞ በሃገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በህገወጥ መንገድ ገብተው የተያዙ ናቸው።

እነዚህ ኢትዮጵያውያን ደቡብ አፍሪካ ለመድረስ ኬንያን፣ ታንዛኒያንና ሌሎች ሃገራትን በማቋረጥ ረጅም ጉዞ ያደረጉ ሲሆን ከፍተኛ ገንዘብ ላሸጋጋሪዎች መክፈላቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እየከፋ በመጣው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የተነሳ በየቀኑ በሲዎች የሚቆጠቱ ኢትዮጵያውይን በአራቱም አቅጣጭእዎች ሃገር ጥለው እንደሚሰደዱ መረጃዎች ያመለክታሉ።