ገዥው ፓርቲ ባህርዳር ላይ  የግዳጅ ሰልፍ ሊጠራ ነው።

ታኀሳስ ፲፯(አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግ   ከቀናት በፊት በባህርዳር የተካሄደውንና  ምእመናን የተገደሉበትን የተቃውሞ ሰልፍ – የሚቃወም  ሌላ የግዳጅ ሰልፍ  ሊጠራ መሆኑን የከተማው ነዋሪዎች  ገለጹ።

እንደ ምንጮች ገለጻ በግዳጁ ሰልፍ የማይገኝ የባህርዳር ነዋሪ ቅጣት ይጣልበታል ተብሏል።

ገዥው ፓርቲ በአማራ ክልል አስተዳደር ባህር ዳር ከተማ የቤተ ክርስቲያን ንብረት የሆነውን የታቦት ማደሪያ ለመንገድና ለጥቃቅንና አነስተኛ ሱቆች መስሪያ እንዲነጠቅ ማዘዙን ተከትሎ የባህር ዳር  ህዝበ-ክርስቲያን የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸው ይታወቃል።

በሰልፉ ሰላማዊ ሰዎች ከመገደላቸውም ባሻገር በርካቶች መጎዳታቸው በምእመናኑ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣና ቅሬታ  በቀሰቀሰበት በአሁኑ ወቅት ገዥው ፓርቲ ቀደም ሲል የተካሄደውን ህዝባዊ ተቃውሞ ሰልፍ የሚቃወም  ሌላ የድጋፍ ሰልፍ ሊጠራ መሆኑን የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ ያመለክታል።

መንግስት ታህሳስ 9/2007 ዓ.ም የተደረገውን ህዝባዊ ተቃውሞ የ‹‹ፀረ ሰላም ኃይሎች እጅ እንዳለበት›› በመግለጽ ‹‹ህገ-ወጥ ሰልፍ›› ማለቱ  ይታወሳል።

በአሁኑ ወቅት  ባህር ዳር ከተማ የሚገኙት የቀበሌ ካድሬዎች የኢህአዴግን የግዳጅ ሰልፍ ለማሳካት   እያስተባበሩ እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቀበሌ ካድሬዎች በየ ቤቱ እየሄዱ የነዋሪዎችን ስም በመመዝገብ በሰልፉ የማይሳተፍ ሰው ቅጣት እንደሚጠብቀው እያስጠነቀቁ  እንደሆነ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

የግዳጅ ሰልፉ ታህሳስ 21 ወይንም 22 ቀን 2007 ዓ.ም ይደረጋል ተብሎ ይታሰባል፡፡