የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር በ15 ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎችን ሊያደርግ ነው

ታኀሳስ ፲፯(አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-የ9ኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትብብር ‹‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› በሚል ያወጣውን ሁለተኛ ዙር መርሃ ግብሩን ታህሳስ 17 ቀን 2007 ዓ.ም ይፋ ሲያደርግ፣ ሁለተኛ ዙር መርሃ ግብሩም ለ2 ወራት የሚቆይ እንደሚሆን አስታውቋል።

የትብብሩ አመራሮች በሰማያዊ ጽ/ቤት የሰጡትን  መግለጫ ተንተርሶ ነገረ ኢትዮጵያ እንደዘገበው በሁለተኛ ዙር የትብብሩ መርሃ ግብር መሰረት የካቲት 15 ቀን 2007 ዓ.ም በተመሳሳይ ሰዓት በ15 የሀገሪቱ ትላልቅ ከተሞች ላይ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፎች ይደረጋሉ።  በአዲስ አበባ፣ በሀዋሳ፣ በባህር ዳርና በአዳማ ደግሞ ህዝባዊ ስብሰባዎች እንደሚደረጉ የትብብሩና የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ይልቃል ጌትነት (ኢ/ር) በመግለጫው ወቅት ተናግረዋል፡፡

ይህን የሁለተኛ ዙር የሁለት ወር ዕቅድ ከታህሳስ 16 እስከ የካቲት 15 /2007 አውጥቶ በቀዳሚነት ለዋነኛ ባለቤቶቹና ፈጻሚዎቹ ኢትዮጵያዊያን ሲያቀርብ እንደመጀመሪያው ዙር ከጎኑ እንደሚቆሙ ሙሉ እምነት በማሳደር ነው›› ያለው መግለጫው፣ በትብብሩ በኩል በአመራር ከፊት ቆመው ትግሉን ለመምራት ዝግጁነትና ቁርጠኝነት መኖሩን ሊቀመንበሩ አስረድተዋል።

የትብብሩ አስተባባሪ ኮሚቴ ለእንቅስቃሴው ማስፈጸሚያ 1 ሚሊየን 200 መቶ 15 ሺህ  ብር በጀት አጽድቋል። በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከጎኑ እንዲቆሙ ትብብሩ ጥሪውን  አስተላልፏል፡፡