ዶክተር ዓቢይና የለውጥ ቡድናቸው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በመቆም በሚያደርጉት ትግል አብረናቸው መሆናችንን ልናረጋግጥላቸው እንወዳለን ሲል አርበኞች ግንቦት ሰባት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ምላሽ ሰጠ።
(ኢሳት ዜና ሰኔ 13 ቀን 2010 ዓ/ም) “የሰለጠነ ፓለቲካ” የምንመርጠው፣ የምናውቀውና የምንመኘው የትግል ስልት ነው” በሚል ርዕስ አርበኞች ግንቦት ሰባት ዛሬ ባወጣው መግለጫ ፣ ዶክተር አብይ አህመድ ለምክር ቤት ያቀረቡትን የሥራ ዘገባ እና ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ በአንክሮ እንደተከታተለው በመጥቀስ፣ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢህአዴግ መንግሥት የፀጥታና የደህንነት ኃይሎች የአሸባሪነት ተግባራትን የሚፈጽሙ እንደሆኑ በይፋ ከመናገራቸውም ባሻገር ፤ ፓርቲና መንግሥት ተቀላቅለው ነፃ ተቋማት እንዳይኖሩ መደረጉን እና የዳኝነት ሥርዓቱ ከፍተኛ ችግር ያለበት መሆኑን መግለጻቸውን አድንቋል።
“ንቅናቄዓችን ለዓመታት ሲናገር የነበረውን ሀቅ እሳቸው መናገራቸው፣ በአንድ በኩል እሳቸው በግላቸው ከእውነት ጎን ለመቆም ያላቸውን ቁርጠኝነት ሲያመለክት -በሌላ በኩል ደግሞ እሳቸው የሚመሩት የለውጥ ቡድን ለሀገራዊ መግባባት እያሳየ ያለው ዝግጁነት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ያመለክታል የሚል እምነት አሳድሮብናል” ብሏል ንቅናቄው።
” እነዚህ ቀድሞ ሲካዱ የነበሩ እውነታዎች በእርሳቸው አንደበት በምክር ቤቱ ስብሰባ መገለፃቸው፣ እስካሁን ሲፈፀሙ የነበሩ በደሎችን ለማስቀረት እና ጉድለቶችን ለማረም ብርቱ ፍላጎት እንዳላቸው ያሳያል ብለን እናምናለን” ያለው ንቅናቄው፣ ዶ/ር ዓቢይ እስካዛሬ በኢትዮጵያ የምክር ቤት ታሪክ ውስጥ ያልታየ ሀቀኝነት በማሳየታቸውም አድናቆቻችን ከፍተኛ ነው”ሲል ግልጿል።
እንደ አርበኞች ግንቦት በሥራ ላይ ያለውንና ቋንቋን መሠረት ያደረገውን የክልል አስተዳደራዊ መዋቅር በተመለከተ የተናገሩትም ትኩረት የሚስብ ነው።
በተለይ ቋንቋን መሠረት ያደረገ ማካለል በየቦታው ለሚነሱ የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎች አስተዋጽኦ ማበርከቱን፤ የሕዝብ መፈናቀልና መገፋት ማስከተሉን፤ ዘረኝነትን በማባባስ በሀገራችን ውስጥ በአስደንጋጭ ሁኔታ ግጭት እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ ማበርከቱን እና ክፍለ አህጉራዊ እይታን ነስቶ ዜጎች ስለመንደራቸው ወሰን አብዝተው እንዲጨነቁ ማድረጉን የሚገልጸው የንግግራቸው ክፍል- ለአብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ የሰጠ እና የወደፊት መንገዳቸውን አመላካች ተደርጎ እንደተወሰደ ንቅናቄው አመልክቷል።
“አሁን ያለው የፌደራል አወቃቀር መሠረቱ ቋንቋ ነው ይባል እንጂ በተግባር የሚታየው ግን ዘር ነው።”ያለው አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ ይህ አደረጃጀት ለኢፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል፤ አድልዎ ለተሞላበት አስተዳደርና ለሚሊዮች መፈናቀል ምክንያት ሆኖ መቆየቱን አትቷል።
ዶ/ር ዓቢይ ቋንቋን መሠረት ያደረገ የፌደራል አወቃቀር ያስገኛቸውን ጥቅሞችና ጉዳቶችን መዝኖ አማራጭ የአደረጃጀት ንድፎችን የሚያዘጋጅ ኮሚሽን የሚዋቀር መሆኑን መግለፃቸውም- አርበኞች ግንቦት 7 የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄን (አርበኞች ግንቦት 7) በእጅጉ አስደስቷል ያለው አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ በዚህ ረገድ ንቅናቄያችን የበኩሉን ለማበርከት ዝግጁነቱን ይገልፃል ብሏል።
ዶ/ር ዓቢይ አህመድ ህወሓትንና የትግራይ ሕዝብን ለያይቶ ስለመመልከት የተናገሩትም ንቅናቄዓችን ከልብ የሚያምንበትና በጽናት ሲያራምደው የቆየው እምነት ነው ሲልም አርበኞች ግንቦት ሰባት አመልክቷል።
“ ህወሓት በርካታ አኩይ ተግባራትን የፈጸመ፤ የአገዛዙን የደህንነትና የፀጥታ ተቋማትን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር የሚቃወሙትን ሁሉ እስር ቤት በማጎር በፈጸመው ሰቆቃ- በርካታ ዜጎችን ለኣካልና ለስነልቦና ጉዳት የዳረገ፤ ሺዎችን የገደለና ሚሊዮኖችን ለስደት የዳረገ፤ የመንግሥት ሥልጣንን ለሀብት ዘረፋ መጠቀምን ብቸኛ አማራጭ ያደረገ ፍጹም አምባገነንና ዘራፊ ድርጅት ነው።” ያለው ንቅናቄው፣ “ይህ ድርጅት በነፃ ምርጫ ሳይመረጥ የትግራይ ሕዝብ ተወካይ ነኝ ማለቱ ሳያንስ ራሱን ከትግራይ ሕዝብ ጋር እኩል አድርጎ የሚያቀርብ ትዕቢተኛ ድርጅት ነው።”ሲልክ ከሷል።
“ በዚህም ተግባሩም የትግራይን ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ አራርቆታል። ይህ ከእንግዲህ መቆም አለበት።” ያለው አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ ለዚህም ነው ሕዝብንና ድርጅትን የመለየት አስፈላጊነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ መገለፁን እጅግ በጣም ጥሩ ነገር ነው ብለን ያመንነው ብሏል።
ይህ መልዕክት ለትግራይ ብቻ ሳይሆን በፍትሃዊና ነፃ ምርጫ ተመርጠው ሳያሸንፉ የሕዝብ ተጠሪ ነኝ የሚሉ ድርጅቶችን ሁሉ የሚመለከት ነው ብለን እናምናለን ሲልም ንቅናቄው አሣስቧል።
“ ህወሓትን በተመለከተ ጥቂት ተጨማሪ ነገር ማውሳት የምንፈልገው-ህወሓትን የምንታገለው ከትግራይ ሕዝብ ጎን ቆመን መሆኑን ነው። ይህ ብቻ ሳይሖን በራሱ በህወሓት ውስጥም የለውጥ ኃይሎች መኖራቸውን ጠንቅቀን እናውቃለን። የኢትዮጵያን ሰቆቃ በመቀነስ ረገድ የእነዚህ ህወሓት ውስጥ ያሉ የለውጥ አራማጆች ሚና ከፍተኛ ነው ብለንም እናምናለን። ስለሆነም፣ ከእነዚህ ወገኖች ጋር ተባብረን ለመሥራት ዝግጁዎች ነን።” ሲልም አርበኞች ግንቦት ሰባት ገልጿል።
በመገዳደል ሥልጣን መያዝም ሆነ በስልጣን ላይ መቆየት ጊዜው ያለፈበት “ኋላ ቀር ፓለቲካ” እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ገለጻ የአርበኞች ግንቦት 7 የቆየ እምነት እንደሆነም አውስቷል።
አርበኞች ግንቦት 7 የመሣሪያ ትግል ዋነኛ የትግል ስትራቴጅው አድርጎ፤ በዚህ መንገድ የፓለቲካ ስልጣን የመያዝ ዓላማ ኖሮት አያውቅም። ሆኖም ግን እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ገጥሞን የነበረው ባላንጣ የኋላ ቀር ፓለቲካ ቀንደኛ አራማጅ የነበረ በመሆኑ ፣ዜጎች አገዛዙ ከሚያደርስባቸው ሽብር ራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን፣ ድርጅታቸውን፣ ማኅበረሰባቸውንና ፓለቲካዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን እንዲከላከሉ ሲያበረታታ ቆይቷል። ራስን ከጉልበተኛ አጥቂ መከላከል፣ ፍትሀዊ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮዓዊ መብት ነው፤ አጥቂ ከሌለ ግን ይህ አያስፈልግም ብሏል ንቅናቄው።
ዶ/ር ዓቢይ አህመድና የለውጥ ቡድናቸው ተስፋ እየሰጡ ባሉበት መንገድ ኢትዮጵያን መርተው ዜጎችን የሚያሸብር አገዛዝ እንዳይኖር የሚያደርጉ ከሆነ፤ የሰለጠነ ፖለቲካ እንዲካሄድ የሚያስፈልጉ እርምጃዎችን በተግባር መውሰዳቸውን ከቀጠሉ፤ የህወሓት አገዛዝ ለነፃነትና ለዴሞክራሲ የሚታገሉ ኃይሎች ላይ በፓርላማ አስጸድቆ ያሳወጀውን የሽብርተኝነት ፍረጃ ካነሱ፤ ለዲሞክራሲ መስፈን እንቅፋት የሚሆኑ ሌሎች ህጎች ከተሻሩ እና ነፃ ተቋማት እንዲመሠረቱ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ከተጀመሩ አርበኞች ግንቦት 7 ራስን በመከላከል ተግባር ላይ ሕይወት፣ ጊዜና ንብረት የሚያጠፋበት ምንም ምክንያት የለውም። ምክንያቱም የሰለጠነ ፓለቲካ የምንፈልገውና ለሀገራችን የምንመኘው የትግል ስልት ነው ሲልም አክሏል።
ንቅናቄው አክሎም ዶ/ር ዓብይ በመግለጫቸው ይህንን የለውጥ ሂደት ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ኃይሎች እየፈጸሙ ያለውን አሻጥር ነቅቶ መጠበቅ እንደሚገባና ቅልበሳውንም ለመከላከል የማኅበረሰቡን ሰፊ ድጋፍና ተሳትፎ እንደሚፈልግ መናገራቸው፤ እኛም እንደ ድርጅት ስናስጠነቅቅ የነበረውና እንዲህ ዓይነት ቅልበሳን ለመከላከል በኢህአዴግ ውስጥ ካሉ የለውጥ ኃይሎች ጋር ሙሉ ትብብር እንደምናደርግ ከዚህ በፊት ያሳወቅነውን አሁንም በግልጽ ደግመን እናሳውቃለን ብሏል።
ይህ የለውጥ ሂደት ግቡን እንዲመታና ከዚህ ሂደት የሚወጣው የፖለቲካ ሥርዓት ሰፋ ያለ ማኅበራዊ ተቀባይነት እንዲኖረው ሰፋ ያሉ የፖለቲካና የሲቪክ ማኅበረሰብ ኃይሎች የሚሳተፉበት ሀገራዊ ውይይት በቶሎ የመደረጉን አስፈላጊነት አሁንም በድጋሚ በአንክሮ ማሳሰብ እንፈልጋለን ያለው አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ በእንዲህ ዓይነት ውይይትም ድርጅታችንም ሆነ ከድርጅታችን ጋር ተባብረው የሚሠሩ የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶች የሚጠበቅብንን ሙሉና ቀና ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን ብሏል።
ንቅናቄው መግለጫውን ሲቋጭም -አርበኞች ግንቦት 7 ራሱ፣ በታሪካችን ውስጥ እስካሁን ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ እውነተኛ ፉክክር የታየበት የምርጫ 97 ውጤት ነው። የአርበኞች ግንቦት 7 አመራርና አባላት በምርጫ 97ቱ የሰለጠነ ፓለቲካ ተሳትፎ ያደረጉ ዜጎች መሆናቸውን ኢትዮጵያዊያን ያውቃሉ። የንቅናቄዓችን ተልዕኮም በግንቦት 7 ቀን 1997 ለአጭር ጊዜ አጣጥመን በጉልበት የተነጠቅነው የሰለጠነ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ህጋዊ የፓለቲካ ስልጣን ሽግግርና በዚህም ሂደት የሀገሪቱን አንድነትና የሕዝቡን አብሮነት ያስጠበቀ፤ የሁሉንም የሀገራችንን ዜጎች እኩልነት ያስረገጠ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሥርዓት እውን ማድረግ ነው።ስለሆነም ዜጎች ላይ የሚደርስ ግልጽ ጥቃት እስከሌለ ድረስ ራስን በመከላከል ላይ ሕይወት፣ ጊዜ፣ ጉልበትና እውቀትን ማባከን ምርጫችን አለመሆኑ እንገልፃለን። ብሏል።