(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 15/2010)
የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ዶክተር አብይ አሕመድን የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ።
አቶ ለማ መገርሳን ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ ከፓርቲ ሃላፊነታቸው ዝቅ አድርጓቸዋል።
የዶክተር አብይ አህመድ በኦሕዴድ ሊቀመንበርነት መመረጥ ምናልባትም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በእጩነት እንዲቀርቡ ያስችላቸዋል።
ዶክተር አብይ አህመድ የፓርላማ አባል በመሆናቸው ኦሕዴድ የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ የመረጠው ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እጩ አድርጎ ለማቅረብ እንደሆነ የፖለቲካ ምሁራን ይናገራሉ።በአሁኑ የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የሽግሽግ ምርጫ አቶ ለማ መገርሳ የክልሉ ፕሬዝዳንት እንደሆኑ ይቀጥላሉ ተብሏል።የአመራር ምደባ ማስተካከያው በኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መጽደቁን ድርጅቱ ገልጿል።የዶክተር አብይ አህመድ ግለ ታሪክ እንደሚያሳየው ኦህዴድን የተቀላቀሉት በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው።ከፖለቲካ ተሳትፏቸው ጋር ተያይዞ በወታደራዊ ተቋም ውስጥ ያገለግሉት ዶክተር አብይ አሕመድ የሌተናል ኮሎኔል ማዕረግም አላቸው።በዚሁ ማዕረጋቸውም በተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮን ለማስፈጸም ሩዋንዳ እንደዘመቱም ነው የሚነገረው።ከ2002 ጀምሮ የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነውም ተመርጠዋል።ከ2007 ጀምሮ ደግሞ የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ።ዶክተር አብይ ከ2000 እስከ 2003 ድረስ የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ/ኢንሳ/መስራችና ዳይሬክተርም በመሆን አገልግለዋል።ዶክተር አብይ ለቀጣዩ የጠቅላይ ሚኒስትር ምርጫ ከወዲሁ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት አቶ ለማ መገርሳን ተክተው የኦሕዴድ ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል።ይህ እውን እንዲሆን ግን በቀጣይ የኢሕአዴግ ምክር ቤት የግምባሩ ሊቀመንበር ሆነው መመረጥ ይኖርባቸዋል።