ዶክተር አብይ በፓርላማ ያቀረቧቸው 10 ሚኒስትሮች ሹመት ጸደቀ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 11/2010) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ዛሬ በፓርላማ ያቀረቧቸው 10 ሚኒስትሮች ሹመት ጸድቋል።

የነበሩት ሚኒስትሮች በከፊል ሲባረሩ ፣የተወሰኑት ባሉበት ቀጥለዋል።

የቀሩትም የሚኒስትር መስሪያ ቤት ቀይረው በሃላፊነት እንዲቀጥሉ ተወስኗል።

በኢሕአዴግ የስልጣን ዘመን የሚኒስትሮቹ የትውልድ ቦታ እንጂ ብሔራቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ያልተገለጸበት ካቢኔ ብዙ አዲስ ፊት አልታየበትም ተብሏል።

ከስልጣናቸው የተነሱት ሚኒስትሮች የእንስሳትና አሳ ሀባት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ፣የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትር ዶክተር ኢያሱ አብርሃ፣የንግድ ሚኒስትሩ ዶክተር በቀለ ቡላዶ፣ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ፣የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ ደምቱ ሃምቢሳ ፣የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሃላፊ አቶ  ከበደ ጫኔና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ መሆናቸው ታውቋል ።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነም ከሃላፊነታቸው ተነስተዋል።

ቦታቸውም በዶክተር አሚር አማን ተተክቷል።

በንግድ ሚኒስትሩ በዶክተር በቀለ ቡላዶ ምትክ አቶ መላኩ አለበል ሲሾሙ፣በጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ጌታቸው አምባዬ ቦታ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ስልጣን ይዘዋል።

በሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ደሚቱ ሐምቢሳ ምትክ ወይዘሮ ያለም ጸጋዬ ሲሾሙ፣በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በአቶ ከበደ ጫኔ ቦታ አቶ ኡመር ሑሴን ተሹመዋል።

የመንግስት የልማት ድርጅት ሚኒስትር በነበሩት በዶክተር ግርማ አመንቴ ምትክ በቤልጂየም የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አቶ ተሾመ ቶጋ ተሰይመዋል።

ዶክተር ግርማ አመንቴ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሹመት አግኝተዋል፣የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ የነበሩት ዶክተር ነገሬ ሌንጮም የኦሮሚያ ክልል የኮሚኒኬስን ጉዳዮች ሃላፊ ሆነው መሾማቸው ታውቋል።

ወደ ትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንትነት በሒዱት በኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ምትክ ወይዘሮ ኡባ መሃመድ ተሹመዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ወደ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሃላፊነት ሲዛወሩ የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ እሳቸውን ተክተው የትራንስፖርት ሚኒስትር ሆነዋል።

የማዕድን፣ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ደግሞ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነዋል።በማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትርነትን ደግሞ  አቶ መለሰ አለሙ ወሰደዋል።

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር አምባቸው መኮንን የኢንደስትሪ ሚኒስትር ሆነዋል።አቶ ዣንጥራር አባይ ደግሞ ዶክተር አምባቸውን ተክተው የከተማና ቤቶች ሚኒስትር መሆናቸው ተመልክቷል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር ሒሩት ወልደማርያም ወደ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሲዛወሩ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን እሳቸውን ተክተው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሆነዋል።

በፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነና በዶክተር ኢያሱ አብርሃ የተያዙት ሁለት ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች በአንድነት ተጣምረው በሁለቱ ባለስልጣናት ምትክ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የግብርና እና የእንስሳት ሃብት ሚኒስትር ተደርገዋል።

በነበሩበት የሚኒስትርነት የስልጣን ቦታቸው የቀጠሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፣የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም ተከስተ፣የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ፣የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ሚኒስሩር አቶ ታገሰ ጫፎ፣የኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ አህመድ ናቸው።

የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ በቀለ፣የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዶክተር ገመዳ ዳሌ በነበሩበት ቀጥለዋል።

አዲሱ ካቢኔ ብዙም አዲስ ፊት አልታየበትም ተብሏል።

የድርጅት ሰዎች መልሰው ሃላፊነት የያዙበት እንደሆነም ተመልክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር አብይ አሕመድ ተሿሚዎቹን ሲያስተዋዉቁ የትውልድ ቦታቸውን እንጂ ብሔረሰባቸውን አለመጥቀሳቸው በኢሕአዴግ የ27 አመታት አገዛዝ አዲስ ክስተት ሆኗል።

ይህ በእንዲሕ እንዳለም አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ ተነስተው በምትካቸው ወይዘሮ ሙፍርያት ካሚል አፈጉባኤ ሆነው ተሹመዋል።