የጠ/ሚኒስትሩ አዲስ ሹመት ህዝቡን እያነጋገረ ነው

የጠ/ሚኒስትሩ አዲስ ሹመት ህዝቡን እያነጋገረ ነው
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 11 ቀን 2010 ዓ/ም) በኢትዮጵያ የተነሳውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጡት ዶ/ር አብይ አህመድ አዳዲስ ሚንስትሮችና ምክትል ሚኒስትሮችን የሾሙ ቢሆንም፣ ሹመቱ ህዝቡን እያነጋገረ ነው። ነባሩ አመራር ተመልሶ መምጣቱን የሚያነሱ ወገኖች የመኖራቸውን ያክል ህወሃትን በኦህዴድ የመተካት እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው የሚል ትችት የሚሰነዝሩ ሰዎችም አሉ።
አዲሱ ጠ/ሚኒስትር 6 ነባር ሚኒስትሮችን ወደ ሌሎች ሚኒስትሪዎች ማሸጋሸጋቸውን ሲገልጹ፣ 10 ደግሞ አዳዲስ ሚኒስትሮችን ሹመዋል። አዳዲስ ፊቶችን ማየት የሚፈልጉ ሰዎች ሽፈራው ሽጉጤና ሲራጅ ፈርጌሳ ተመልሰው መሾማቸውን ተችተዋል። አቶ ሽፈራው የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ፣ ለረጅም አመታት የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ ደግሞ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሆነዋል።
የኦህዴዱ አቶ ኡመር ሁሴን፣ የኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲሾሙ በዶ/ር ደብረጺዮን ከብረሚካኤል ቦታ የተሾሙት የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ኡባ ሙሃመድ ደግሞ ከስራው ጋር ምንም እውቅናና ልምድ የሌላቸው ሰው መሆናቸውን ግለሰቧን በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች ተናግረዋል። በዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ቦታ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ ሆነው የተሾሙት አቶ አህመድ ሼዲ ከአቶ አብዲ ኤሌ ጋር በመሆን በወንጀል መጠየቅ ሲገባቸው ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውን የሶማሊ ክልል ተወላጆች ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
ከሚንስትሮች በተጨማሪ በምክትል ሚኒስትርና በአማካሪነት የተሾሙትም ግለሰቦች የትችት ምንጭ ሆነዋል። በህወሃቶች ተይዞ የነበረው የጠ/ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ቦታ በቀድሞው አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ የተያዘ ሲሆን፣ ኦህዴድ መከላከያውን እና የደህንነት አማካሪ ቦታውን እንዲሁም ውጭ ጉዳይ መስሪያቤቱን መያዙ የህወሃት አይነት መንገድ በመከተል ስልጣኑን በበላይነት የማስጠበቅ ስራ እየሰራ ነውን የሚል ትችት አስከትሎበታል። የመከላከያ ኢታማዦር ሹሙ ጄ/ል ሳሞራ የኑስና የደህንነት መስሪያ ቤቱ ዋና አዛዥ አቶ ጌታቸው አሰፋ ከስልጣናቸው ይነሱ አይነሱ የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ እነዚህ ሰዎች የሚተኩ ከሆነ የህወሃት የበላይነት ማክተሙን የሚያመላክት ይሆናል የሚል አስተያየቶችም በማህበራዊ ሚዲያዎች እየቀረቡ ነው። እነዚህ ሰዎች የሚተኩ ከሆነ በማን ይተካሉ የሚለውም ሌላ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል።
በህወሃቶች ቁጥጥር ስር የቆየውና ከፍተኛ የገንዘብ ዝርፊያ ሲፈጸምበት የቆየው ሜቴክ ከጄኔራል ክንፈ ዳኘው እጅ ወጥቶ በዶ/ር በቀለ ቡላዶ እንዲያዝ ተደርጓል። ጄ/ል ክንፈ ቀደም ብለው የስልጣን መልቀቂያ አስገብተው እንደነበር ተዘግቧል።
ከጅምሩ ጀምሮ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሆነው የሰሩትና የዶ/ር አበይ አህመድ ዋና ባላንጣ ተደርገው የሚቆጠሩት ሜ/ጀነራል ተክለብርሃን ወልዳረጋይ በአቶ ተመስገን ጥሩነህ የተተኩ ሲሆን፣ ጄ/ሉ ዶ/ር አብይ እንዳይመረጡ ከፍተኛ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የቆዩ ናቸው። ዶ/ር አብይ እንደተመረጡም የስልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ አቅርበው ነበር።
ጠ/ሚኒስትሩ እያስተቻቸው ያለው ሌላው ሹመት የህወሃቷን ም/ል ሊመንበር ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር የዴምክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ ሆነው መሾማቸው ነው። ጠ/ሚኒስትሩ አዲስ የዲሞክራሲ ስርዓት እንደሚገነባ በመጀመሪያ የፓርላማ ንግግራቸው ቃል የገቡት በወ/ሮ ፈትለወርቅ ሹመት አፈር በልቷል የሚሉ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።
በአማራው ህዝብ ከፍተኛ ተቃውሞ የሚቀርብባቸውና በህዝቡ ላይ የዘለፋ ቃላትን በመወርወራቸው የሚነቀፉት አቶ አለምነው መኮንን በሚኒስትር ማዕረግ የመለስ ዜናዊ የአመራር አካዳሚ ፕሬዚዳንት ሆነው መሸማቸው ግለሰቡ ለመለስ ዜናዊ ካላቸው አድናቆት አንጻር ትክክለኛ ቦታቸውን አግኝተዋል የሚሉ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።
የፖሊስ ኮሚሽነር አሰፋ አብዩ በአቶ ያሬድ ዘሪሁን ተተክተዋል።
ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ደግሞ አባ ዱላ ገመዳን ተክተው የተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባዔ ሆነው ተሹመዋል።