(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 16/2010)የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የዚምባቡዌውን ሮበርት ሙጋቤን የበጎ ፈቃድ አምባሳደር አድርገው የሾሙበት ድርጊት እንዲመረመርና ጉዳዩ ሙስና ሆኖ ከተገኘ ስልጣናቸውን እንዲለቁ ተጠየቁ።
ቻይና ስፍራውን እንዲያገኙ ለተጫወተችው ሚና የተሰጠ ምላሽ ይሆን ወይ የሚሉ መላምቶች መንጸባረቃቸውንም በዋሽንግተን ፖስት ላይ ጥቅምት 25/2017 የቀረበው ጽሁፍ አመልክቷል።
ለ18 አመታት የሲ ኤን ኤን ዘጋቢና ተንታኝ የነበረችውና በአሁኑ ወቅትም በዋሽንግተን ፖስት፣በቺካጎ ትሪቡንና መሰል ታዋቂ ጋዜጦች ላይ ትንታኔዎችን በመጻፍ ትታወቃለች ፍሪዳ ጊቲስ።
እናም ዘጋቢዋ ጥቅምት 25/2017 በታተመው ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ላይ ባቀረበችው ጽሁፍ የዶክተር ቴድሮስን ርምጃ ባለጸጋይቱን ሀገር ዚምባብዌን ኢኮኖሚ ላደቀቀ አምባገነን አዛውንት የቀረበ ሽልማት በማለት አውግዛለች።
በጤናውም ዘርፍ ሙጋቤ ለሀገራቸው ያደረጉት አስተዋጽኦ የለም ስትልም ተችታለች።
አሜሪካ የዶክተር ቴድሮስ ርምጃን ማውገዟ፣የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር የሚያሳዝን ቀልድ መስሏቸው እንደነበር የተነገሩትን በጽሁፏ ያካተተችው ፍሪዳ ጊትስ፣የአየር ላንድ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ድርጊቱን ትንኮሳና አስደንጋጭ ሲሉ መናገራቸውንም በዚሁ በዋሽንግተን ፖስት ዘገባዋ ላይ አስፍራለች።
የአለም ጤና ድርጅት ሰራተኛ ዶክተር ቴድሮስ በተቋሙ ተአማኒነትና የገንዘብ ምንጭ ላይ የሚያደርሰውን ተጽእኖ ሊታያቸው ይገባ ነበር ሲሉም መተቸታቸውም ተጠቅሷል።
የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የፈጸሙት ድርጊት አለም አቀፉን ተቋም ጥያቄ ውስጥ ማስገባቱን ፍሪዳ ጊቲስ ገልጻለች።
ከዚህ ድርጊት በስተጀርባ ምን እንዳለ ግን ሊመረመር እንደሚገባ አስገንዝባለች።
ይህ ርምጃ ከሙስና ጋር የተያያዘ ሆኖ ከተገኘም ዶክተር ቴድሮስ በአስቸኳይ ስልጣናቸውን መልቀቅ ይገባቸዋል ስትል ጥሪ አቅርባለች።
የተባበሩት መንግስታት ጉዳዮችን የሚመረምረው ዩኤን ዋች ዳይሬክተር ሂለር ኒውር ይህ ሹመት ለሆነ ነገር የተሰጠ ማካካሻ ካልሆነ በእርግጥ ሽልማት ነው በማለት ከሹመቱ በስተጀርባ አንዳች ነገር ሊኖር ይችላል የሚል ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል።
ቴድሮስ ለአለም ጤና ድርጅት እንዲታጩ በወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ሮበርት ሙጋቤ ድጋፍ ስላደረጉላቸው በምላሹ የተሰጠ ሽልማት ይሆን ሲሉም ጠይቀዋል።
ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በኢትዮጵያ በጤና ጥበቃ ሚኒስትርነታቸው ወቅት ውጤታማ ቢሆኑም በማሰቃየት፣በጭቆናና በምርጫ ማጭበርበር የታወቀ አምባገነን መንግስት ውስጥ ትልቅ ሚና የነበራቸው እንደነበሩም ጽሁፉ በዝርዝር አስቀምጧል።
ሙጋቤን የአለም ጤና ድርጅት አምባሳደር አድርገው ሲሾሙ እንዲመረጡ ከፍተኛ ድጋፍ ላደረገችላቸው ቻይና ውለታ እየመለሱ ይሆን የሚል ጥርጣሬ መከተሉንም በጽሁፉ ተመልክቷል።
ቻይና ተጽእኖዋን ወደ አለም አቀፍ መድረክ የማስፋት ፍላጎት እንዳላት ፕሬዝዳንቱ መናገራቸውንም ጽሁፉ ያስታውሳል።
ከምዕራቡ አለም የተገለሉትን የዚምባቡዌውን ሮበርት ሙጋቤን በከፍተኛ ደረጃ የምትደግፈውም እሷ በመሆኗ ጉዳዩ ከዚህ ጋር የተያያዘ ይሆን ወይ የሚለውም ጥርጣሬ ተያይዞ ተነስቷል።