በኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በድጋሚ ተካሄደ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 16/2010) በኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በድጋሚ ተካሄደ።

በርካታ ቁጥር ባለው የጸጥታ ሃይል ታጅቦ በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የተቃዋሚው እጩ ደጋፊዎች በሚገኙበት የምርጫ አካባቢዎች ግጭት ተከስቶ የአንድ ሰው ሕይወት መጥፋቱ ታውቋል።
በርካታ ሰዎችም ተጎድተዋል።

እንደ ሲ ኤን ኤን ዘገባ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ምርጫው በሰላም የተካሄደ ቢሆንም የተቃዋሚ እጩው ራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎች በሚበዙባቸው አራት የምርጫ አውራጃዎች ግን ግጭት ተከስቷል።

ራይላ ኦዲንጋ ከዛሬው ምርጫ ራሳቸውን ማግለላቸው ይታወቃል።

በተለይ ኪሱሙና ኪቦራ በተባሉ የመዲናዋ ናይሮቢ መንደሮች ተቃዋሚዎች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን በኪስሙ የሚገኝ ሆስፒታል አረጋግጧል።

አራት ሰዎች በተተኮሰባቸው ጥይት ሲቆስሉ 19 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በፖሊስ በተፈጸመባቸው ድብደባ በመጎዳታቸው ሆስፒታል ገብተዋል።

በናይሮቢ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች በፖሊስ ከፍተኛ ጥበቃ ተደርጎላቸው የዋሉ ሲሆን በኪሱሙና በኪባራ ግን ተቃዋሚዎች በፖሊሶች ላይ ድንጋይ የወረወሩ ሲሆን ፖሊስ በአጸፋው በአስለቃሽ ጭስና ውሃ በመርጨት ሰልፈኞቹን ለመበተን ሞክሯል።

የተቃዋሚው እጩ ራይላ ኦዲንጋ ባልተሳተፉበት ምርጫ ተቀማጩ ፕሬዝዳንት ያለጥርጥር እንደሚያሸንፉ ግልጽ ቢሆንም አነስተኛ ድምጽ የተሰጠበት ይህ ምርጫ ግን ሕጋዊ ጋሬጣ እንደሚጠብቀው እየተነገረ ነው።

የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ዋፉላ ቼቡካቲ ከፍተኛ የተቃዋሚ ድምጽ ሰጪዎች በሚገኙባቸው አምስት የምርጫ ወረዳዎች ምርጫው ወደ ቅዳሜ ጥቅምት 18 መዛወሩን አስታውቀዋል።

ሕዝቡን በከፍተኛ ደረጃ ከፋፍሏል በተባለው የኬንያ የምርጫ ሂደትና አፈጻጸም ሀገሪቱን ወደ ሁከትና ብጥብጥ እንዳይመራ እየተሰጋ ነው።

ባለፈው ነሀሴ የተደረገውና ተቀማጩ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ያሸነፉበት ምርጫ ማጭበርበር ተፈጽሞበታል በሚል በጠቅላይ ፍርድ ቤት መሻሩ ይታወሳል።