መስከረም ፳፯(ሃያ ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ሦስተኛው የ ኢህአዴግ ፕሬዚዳንት በመሆን በ አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ምትክ ተሾሙ።
የኢህአዴግ/ኦህዴድ አባል የሆኑት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የዛሬ 12 ዓመት አካባቢ ፕሬዚዳንት ነጋሶ ጊዳዳን በመተካት ሁለተኛው ፕሬዚዳንት እንደሚሆኑ በስፋት የተወራ ቢሆንም፤”ፕሬዚዳንት ሆኖ የሚመረጠው ሰው የማናቸውም ፓርቲ አባል ያልሆነ ገለልተኛ ሰው መሆን አለበት” የሚል መመሪያ በማውጣት የግል እጩ ተወካይ የነበሩትን አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስን ሳይታሰብ በቦታው እንዳስቀመጣቸው ይታወቃል።
በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ሲሠሩ የቆዩት ዶክተር ሙላቱ ተሾመም ከ 12 ዓመታት ቆይታ በሁዋላ ሦስተኛው ፕሬዚዳንት ሆነው ዛሬ በአቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ቦታ እንዲቀመጡ ተደርጓል።
ሦስተኛው ፕሬዚዳንት በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ተገኔ ጌታነህ አማካኝነትም ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።
ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስም ለተመራጩ ፕራዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ስልጣናቸውን አስረክበዋል።
አዲሱ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ከተሾሙ በሁዋላ በህዝብ ተወካዮችና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ፥ ምክር ቤቶቹ የጣሉባቸውን አደራና ሐላፊነት ባላቸው ሙሉ አቅም ለመወጣት ቃል ከመግባታቸውም ባሻገር ለሐገራቸው ህዝብም የሚጠበቅባቸውን በሃላፊት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት የመሆን ፍላጎት እንዳለው በራዲዮ ፋና ከተናገረው አትሌት ሀይሌና በዚሁ ዙሪያ በ ኢቲቪ ኦሮምኛ ፕሮግራም ቀርበው ከተጠየቁት ከንግድ ምክር ቤቷ ፕሬዚዳንት ከወይዘሮ ሙሉ ሰሎሞን መካከል አንድኛቸው ፕሬዚዳንት እንደሚሆኑ በስፋት ሲወራ ቢቆይም፤ የርዕሰ ብሔርን ሹመት ጉዳይ ድርጅታዊ ምስጢር ያደረገው ኢህአዴግ እንደዛሬ 12 አመቱ ሁሉ ሰው ያልገመተውንና ያልጠበቀውን የሹመት ርክክብ አድርጓል።
ኢህአዴግ ይህን ምስጢር ጠባቂነት እንደ ድርጅት ብቃትና ጥንካሬ እንደሚወስደው የዛሬ 12 ዓመት አቶ ግርማ ሲሾሙ አስተያየት የሰቱ አንዲት አባላቱ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
በጊዜው አስተያዬት የሰጡ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ ግን፦”ምንም ቦታው ትርጉም ያለው ሀላፊነት ያለበት ባይሆንም የአገር ርዕሰ ብሔር ሆኖ ስለሚመረጥ ሰው በትንሹ ከ6 ወር በፊት ለህዝቡ በግልጽ መደረግ ይኖርበታል። ተሿሚው የ አገርን ምስል ስለሚወክል ህዝቡ ስለሁዋላ ታሪኩ እና ለ አገሩ ስላለው አመለካከት እያነሳ ሊወያይበት ይገባ ነበር። ኢህአዴግ ይህን ጉዳይ በምስጢር መያዙ የዲሞክራሲ ምሰሶዎች ከሆኑት ከግልጽነትና ከተጠያቂነት አሠራሮች ምን ያህል መራቁን የሚያመላክት እንጂ ጥንካሬውን የሚያሳይ አይደለም” ነው ያሉት።