ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጨምሮ ሁለት ሌሎች ተወዳዳሪዎች ለመጨረሻ ዙር ለአለም ጤና ድርጅት ሃላፊነት መታጨታቸውን ተገለጸ

ኢሳት (ጥር 18 ፥ 2009)

የአለም ጤና ድርጅት ቀጣዩ የድርጅቱ  ሃላፊ ሆነው ለመወዳደር በማጣሪያ ካለፉት አምስት ተወዳዳሪዎች መካከል ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖምና የብሪታኒያ እንዲሁም የፓኪስታን ተፎካካሪዎች ለመጨረሻ ዙር መታጨታቸውን ይፋ አደረገ።

የድርጅቱ 34 የስራ አስፈጻሚ የቦርድ አባላት ከአምስቱ ተወዳደሪዎች መካከል ሶስቱን ለመለየት በዝግ የተካሄደ ለሰዓታት የቆየ ቃለመጠይቅና የድምፅ መስጠት ሂደት ማከናወናቸውን አስታውቋል።

በዚሁ የድምፅ ውጤት መሰረትም በመንግስትና በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ድጋፍ የተቸራቸው ዶ/ር ቴዎድሮስ ለመጨረሻ እጩ ከሁለት ተፎካካሪዎች ጋር መብቃታቸውን የአለም ጤና ድርጅት ገልጿል።

የፓኪስታን ተወዳዳሪ ዶ/ር ሳኒያ ኒሽታር፣ እና የብሪታኒያው ዶ/ር ዴቪድ ናባሮ ለመጨረሻ እጩነት ማለፉን የቻሉ ሲሆነ የድርጅቱ አባል ሃገራት የፊታችን ግንቦት ወር በሚያካሄዱት ልዩ ጉባዔ ድምፅ በመስጠት ከሶስቱ አንዱን ለድርጅቱ ሃላፊነት ይመርጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የጣሊያንና የፈረሳይ ተወዳደሪዎች አነስተኛ ድምፅ በማግኘታቸው ወደ መጨረሻው ዙር ማለፉ ሳይችሉ ቀርተዋል።

የአለም ጤና ድርጅት 194 አባል ሃገራት በአባልነት የያዘ ሲሆን፣ ድርጅቱን ለመምራት አፍሪካ እስካሁን ድረስ ዕድል አለማግኘቱን ለመረዳት ተችሏል። ረቡዕ ዕኩለ ለሊት ድረስ በስዊዘርላንድ መዲና ጄኔቫ በተካሄደው ድምፅ የመስጠት ስነስርዓት የአውሮፓ ሃገራት ለአውሮፕላ ተወካዮች የሰጡት ድምፅ መከፋፈል ፈጥሮ የነበረ ሲሆን፣ ለእጩነት የበቁት የብሪታኒያው ተወካይ በቀጣዩ ምርጫ የአውሮፓ ሃገራት ድምፅ ያለመከፋፈ ያገኛሉ ተብሎ መጠበቁን ስታትኒውስ የተሰኘ የሜዲካል መጽሄት ዘግቧል።