የአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ወታደሮች በ14 ሶማሊያውያን ላይ የፈጸሙትን የግድያ ምርመራ ሪፖርት ይፋ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ኢሳት (ጥር 18 ፥ 2009)

በሶማሊያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች በቅርቡ በ14 ሰላማዊ ሰዎች ላይ የፈጸሙትን ግድያ እየመረመረ የሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ውጤቱን ይፋ እንዲያደርግ ሂውማን ራይትስ ዎች ሃሙስ ጠየቀ።

በህብረቱ የሰላም አስከባሪ ሃይል ስር የተሰማሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሃምሌ ወር ከሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ ከተማ በ37 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የዋርዴንዴ መንገድ ከፍተውታል በተባለ የተኩስ ዕርምጃ 14 ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።

ከተለያዩ አካላት የቀረበን ቅሬታ ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት ግድያው በገለልተኛ ቡድን ማጣራት እንዲያካሄድበት ወስኖ የነበረ ሲሆን፣ ውጤቱ ለስድስት ወር ያህል ለህዝብ ይፋ አለመደረጉ ጥያቄን አስነስቶ ይገኛል።

ከተለያዩ አካላት የቀረበን ቅሬታ ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት ግድያው በገለልተኛ ቡድን ማጣራት እንዲካሄድበት ወስኖ የነበረ ሲሆን፣ ውጤቱ ለስድስት ወር ያህል ለህዝብ ይፋ አለመደረጉ ጥያቄን አስነስቶ ይገኛል።

የሰላም አስከባሪ ቡድኑ ግድያው በተፈጸመበት ወቅት ሰዎቹ የሞቱት በአልሸባብ ታጣቂ ሃይልና በኢትዮጵያ ወታደሮች መካከል በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ መሆኑን ገልጾ እንደነበር ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ታይምስ ጋዜጣ ሃሙስ ዘግቧል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሂውማን ራይስት ዎች በበኩሉ ግድያው በጅምላ የተፈጸመ መሆኑን በመግለጽ የምርመራ ውጤቱ በአስቸኳይ ይፋ እንዲደረግ ጥያቄን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ወታደሮች የተኩስ ዕርምጃውን በወሰዱ ጊዜ በርካታ ሰዎች በመንደሩ ለታመመ አንድ ሰው በጸሎት ላይ እንደነበሩ ሂውማን ራይትስ ዎች እማኞችን ዋቢ በማድረግ አስታውቋል። በድርጅቱ የሰብዓዊ መብት ተመራማሪ የሆኑት ላቲቲያ ባደር የአፍሪካ ህብረትም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት የምርመራ ውጤታቸውን ለህዝብ ይፋ በማድረግ የሰላም አስከባሪ ሃይላቸውን ተጠያቂ የማድረግ ሃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያለ ምንም ማጣራት የጅምላ የተኩስ ዕርምጃ መውሰድ በጦር ወንጀለኝነት የሚያስጠይቅ መሆኑን መርማሪው የአለም አቀፍ ህግን በመጥቀስ ለጋዜጣው አስረድተዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች ፈጽመውታል ስለተባለው ግድያ እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የለም።

የአፍሪካ ህብረት በአዲስ አበባ ማካሄድ የጀመረውን የመሪዎች ጉባዔ ምክንያት በማድረግ ሂውማን ራይትስ ዎች ጥያቄውን ቢያቅርብም ህብረቱ እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የለም።

ኢትዮጵያ በህብረቱ የሰላም አስከባሪ ሃይል ስር ካሰማራቻቸው ከ4ሺ በላይ ወታደሮች በተጨማሪ ቁጥሩ ያልታወቅ ሰራዊትን በሶማሊያ በማሰማራት ከአልሸባብ ጋር ለአመታት በጦርነት ውስጥ መሆኗ ይታወቃል።

የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ነገ በሶማሊያ ጉዳይ ላይ ምክክርን ያካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።