ኢሳት (ሚያዚያ 18 ፥ 2008)
የብሪታኒያው ጠ/ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን በመጋቢት ወር በኢትዮጵያ ያደርጉታል የተባለው ጉብኝት ከአንድ ወር በላይ ሳይካሄድ የቀረበት ምክንያት ሳይታወቅ ቀጥሏል። ሁለም መንግስታት ጉብኝቱ ስለቀረበት ምክንያት የሰጡት መግለጫ የለም። የብሪታኒያው ጠ/ሚ/ር ዴቢድ ካሜሩን፣ በመጪው ሰኔ ወር በኬንያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ በጥር ወር ተገልጾ የነበረ ሲሆን፣ ይኸው የኬንያ ጉብኝት በታቀደው ጊዜ ውስጥ እንደሚካሄድ ይፋዊ መረጃዎች አመልክተዋል።
የብሪታኒያው ጠ/ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን፣ ከሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ሃይመንድና ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ በኢትዮጵያ መንግስት መገናኛ ብዙሃን ጭምር የተዘገበ ሲሆን፣ ጉብኝቱ በመጋቢት ወር 2008 እንደሚካሄድ ተገልጾ ነበር።
ጠ/ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደርጉበታል የተባለው የመጋቢት ወር ቢያልፍም፣ ቀጣዩ ወር ሚያዚያ በመገባደድ ላይ ቢሆንም ስለጉብኝቱ ማብራሪያ ሳያገኝ ቀጥሏል።
የብሪታኒያ ጠ/ሚኒስቴር ዴቪድ ካሜሩን በያዝነው 2016 ዓም ጉብኝት የሚያደርጉባቸው ሃገራት ዝርዝር ውስጥ የኢትዮጵያ ጎረቤት ኬንያ እንዳለችበት በዓመቱ መጀመሪያ በጥር ወር ይፋ የተደረገ ቢሆንም፣ ስለኢትዮጵያ ጉብኝታቸው የተጠቀሰው ነገር አልነበረም። የብሪታኒያው የሃገር ውስጥ ጉዳይ ቢሮ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ኦሊቨር ሮቢንስ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር መወያየታቸውን ተከትሎ ዴቪድ ካሜሩን ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ የሚል ዜና መከተሉን መረዳት ተችሏል።
በመጋቢት ወር ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ ተገልጾ፣ ምክንያቱ ሳይጠቀስ ጉብኝታቸው የቀረው ጠ/ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን በጥር ወር ይፋ በሆነው መርሃ ግብር መሰረት በመጪው ሰኔ ወር 2008 በኬንያ የሚያደርጉት ጉብኝት እንደሚካሄድም መረዳት ተችሏል።