በጋምቤላ የተፈጸመውን ግድያ በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ነዋሪዎች እየታሰሩ ነው

ኢሳት (ሚያዚያ 18 ፥ 2008)

በቅርቡ በጋምቤላ ክልል የተፈጸመን ግድያ በማውገዝ በጋምቤላ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍን ያካሄዱ ነዋሪዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እየታሰሩ መሆናቸውን ነዋሪዎች ለኢሳት ገለጹ።

በዚሁ ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት ፎቶግራፍ አንስታችኋል እንዲሁም ሰልፉን አስተባብራችኋል የተባሉ ነዋሪዎች  ቤት ለቤት በመካሄድ ላይ ባለ የእስር ዘመቻ ሰለባ መሆናቸውን እማኞች ገልጸዋል።

የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ባለው እርምጃ ግራ መጋባታቸውን እየገለጹ ያሉት ነዋሪዎች ከሰልፉ ጀርባ እጃቸው ያለበት አካላት ስላሉ በግዳጅ አስታውቁን እየተባሉ ጫና እንደሚደረግባቸውም ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስ አመልክተዋል።

ባለፈው ሳምንት በክልሉ የተፈጸመን ጥቃት በማውገዝ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች በሳምንቱ መገባደጃ ሰላማዊ ሰልፍን በማድረግ መንግስት ጥበቃን እንዲያደርግላቸውና ድርጊቱ የፈጸሙት አካላትም ለህግ እንዲቀርቡ መጠየቃቸው ይታወሳል።

ይሁንና በአካባቢው ተሰማርተው የሚገኙ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ድርጊት በፈጸሙ አካላት ላይ እርምጃን ከመውሰድ ይልቅ ድርጊቱን ባወገዙ ነዋሪዎች ላይ የእስር ዘመቻን እንዲከፍቱ ነዋሪዎቹ አክለው አስረድተዋል።

በኦሮሚያ ክልል ሁከትን አስነስተው የነበሩ አካላት ወደ ጋምቤላ ክልልም ገብተዋል በማለት የጸጥታ ሃይሎች በከተማዋ ተሽከርካሪዎች ጭምር በማስቆም ፍተሻን እያካሄዱ እንደሆነም ለመረዳት ተችሏል።

በርካታ ነጋዴዎችን ጨምሮ ቁጥራቸው በአግባቡ ሊታወቅ ያልቻለ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች በዚሁ የእስር ዘመቻ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንንና ዕርምጃው በከተማው አለመረጋጋት ፈጥሮ እንደሚገኝም እማኞች አክለው ለኢሳት ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በቅርቡ በጋምቤላ ክልል ከ200 በላይ የሆኑ ነዋሪዎች ላይ ግድያን የፈጸሙ አካላት ላይ እርምጃን ለመወሰድ ጥረቱ መቀጠሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

መንግስት ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት ያሉበት ስፍራ ታውቋል ሲል ባለፈው ሳምንት ቢገልጽም  እስካሁን ድረስ የተወሰደ እርምጃ አለመኖሩ ታውቋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ከሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን መግለጫን የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ታፍነው የተወሰዱ ከ100 በላይ ህጻናትን ለማስለቀቅ ጥረቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል ሲሉ ተናግረዋል።