አቶ በቀለ ገርባና ሌሎች ሶስት ሰዎች በቂሊንጦ ምንነቱ ያልታወቀ መድሃኒት እንድንውጥ ተጠየቅን አሉ

ኢሳት (ሚያዚያ 18 ፥ 2008)

ባለፈው ሳምንት ለሁለተኛ ጊዜ የሽብርተኛ ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) አመራርና ሌሎች ሶስት አባላት በቂሊንጦ እስር ቤት የማያውቁትን መድሃኒት እንዲውጡ መጠየቃቸውን ማክሰኞ ለችሎት ገለጹ።

በእስር ቤቱ የቀረበላቸውን መድሃኒት አንውጥም በማለታቸውም ከሌሎች ተከሳሾች ተለይተው ለብቻቸው ለአራት ቀን ያህል በጨለማ ክፍል ውስጥ መቆየታቸውን የፓርቲ አመራት የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ ለፍርድ ቤት አስረድተዋል።

የፓርቲው አመራርን ጨምሮ ሌሎች 22 ግለሰቦች በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ከተቀሰቀሰው ተቃውሞ ጋር እጃችሁ አለበት ተብለው በሽብርተኛ ወንጀል ክስ እንደቀረበባቸው ይታወሳል።

የቀረበባቸውን ክስ ተከትሎም 22ቱ ተከሳሾች ከማዕከላዊ የምርመራ እስር ቤት ወደ ቂሊንጦ እንዲዛወሩ ተደርጎ የነበረ ሲሆን፣ ወደ እስር ቤቱ በተዛወሩ ጊዜም በእስር ቤት አስተዳዳሪዎች አራቱ ተከሳሾች ምንነቱ ያልታወቀ መድሃኒት እንዲውጡ መጠየቃቸውን ለችሎት ገልጸዋል።

ያልታወቀውን መድሃኒት ለመዋጥ ፍቃደኛ ባለመሆናቸውንም በጭለማ ክፍል ለአራት ቀናቶች መቆየታቸውን በቅርቡ ከአራት አመት እስር በኋላ ተለቀው የነበሩት አቶ በቀለ ገርባ ለፍርድ ቤት በአቤቱታ መልክ አቅርበዋል።

ቤተሰቦቻቸው እንዳይጎበኟቸው ተደርገው እንደሚገኙ ያስታወቁት አቶ በቀለ ገርባ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ተመልክቶ እልባት እንዲሰጣቸውና የፍርድ ሂደቱም ለህዝብና ለመገናኛ ብዙሃን ክፍት እንዲሆን ጠይቀዋል።

በጨለማ ክፍል የቆዩትና የፓርቲው አባል የሆኑት አቶ ደጀኔ ጣፋ በበኩላቸው ለሁሉም ተከሳሾች የደህንነት ስጋት መኖሩን በማስረዳት ፍርድ ቤቱ ጉዳያቸውን በአጽንዖት እንዲከታተለው መጠየቃቸውንን ከሃገር ቤት ከተገኘው መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

የተከሳሾች ጠበቃ የሆኑት አቶ ወንድሙ ኢብሳ የኦፌኮ አመራርን ጨምሮ 83 ተከሳሾች በቂሊንጦ እስር ቤት እንደሚገኙ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ይፋ አድርገዋል።

ወደ 97 አካባቢ የሚሆኑ ሌሎች ተከሳሾች ደግሞ በማዕከላዊ አልያም በአዲስ አበባ እስር ቤት እንደሚገኙ ጠበቃው አክለው አስታውቀዋል።

በተከሳሾች ላይ የቀረበን የሽብርተኛ ክስ ለመመልከት የጀመረው ፍርድ ቤቱም የተከሳሾቹን መከላከያ ለመስማት የ15 ቀን ቀጠሮ መስጠቱ ታውቋል።