(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 19/2011)የፌዴራል ስርዓቱ ለክልሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የህልውና ጉዳይ እንደሆነ የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ገለጸ።
ደኢህዴን ህብረብሄራዊነትን የሚያስተናግደውን የፌደራል ስርዓት አጠናክሮ ማስቀጠል የክልሉ መሪ ድርጅት የሁል ጊዜ አጀንዳ ሆኖ እንዲቀጥል በስብሰባው አቅጣጫ አስቀምጧል።
አዳዲስ የክልል ጥያቄዎች የክልሉን መሪ ድርጅት ቀጣይነት፣ ሃገራዊ ነባራዊ ሁኔታ እና የሁሉንም ህዝብ ጥቅም ማዕከል ተደርጎ መታየት እንዳለበት ማዕከላዊ ኮሚቴው ገልጿል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን /ማዕከላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን በፌደራል ስርዓቱና ክልል የመሆን ጥያቄ ላይ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል።
ማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባውን ማጠናቀቁን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፥ ደኢህዴን የፌዴራል ስርዓቱ ለክልሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ያምናል ብሏል።
ስለሆነም ህብረብሔራዊነትን የሚያስተናግደውን የፌደራል ስርዓት አጠናክሮ ማስቀጠል የክልሉ መሪ ድርጅት የሁል ጊዜ አጀንዳ ሆኖ መቀጠል አለበት ነው ያለው።
በክልሉ ውስጥ የሚነሳውን ተጨማሪ ክልል ሆኖ የመደራጀት ጥያቄ መላው የክልሉን ህዝብ በሚጠቅም አኳሃን በተረጋጋና ኃላፊነት በተሞላው ሁኔታ እንዲሁም ዘላቂ መፍትሄ በሚያመጣ መንገድ በድርጅቱ መመራት እንዳለበት መግባባት ላይ ተደርሷል።
እናም እየተነሱ ያሉ አዳዲስ የክልል ጥያቄዎች የክልሉን መሪ ድርጅት ቀጣይነት፣ አገራዊ ነባራዊ ሁኔታ እና የሁሉንም ህዝብ ጥቅም ማዕከል ተደርጎ መታየት እንዳለበት ማዕከላዊ ኮሚቴው ወስኗል።
በደቡብ ክልል የሲዳማ፥ የወላይታ፥የጉራጌ፥የከባታና ጠምባሮ እንዲሁም የከፍቾ ዞኖች እንደ አዲስ ክልል የመሆን ጥያቄ አቅርበው ሕዝበ ወሳኔ እንዲካሄድ በመጠየቅ ላይ ናቸው።
በተለይም ጥያቄው በክልሉ ምክር ቤት ተቀባይነት ያገኝው የሲዳማ ዞን በምርጫ ቦርድ ሕዝበ ወሳኔ እንዲካሄድ ቢጠይቅም ሂደቱ በመዘግይቱ የአካባቢው ሕዝብ ሰላማዊ ሰልፍ እስከማካሄድ ተደርሷል።
ማዕከላዊ ኮሚቴው በመግለጫው በክልሉ ውስጥም ሆነ ከክልል ውጭ የዜጎች ህይወት እና ንብረት ላይ እየደረሰ ያለው አደጋ አስነዋሪና ሊደገም የማይገባው መሆኑንም አሳስቧል።