በሃገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ መካተት ለሚፈልጉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሩ ክፍት ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 20/2011)ኢሕአዴግ ከጥቂት ወራት በኋላ በሚመሰርተው አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ መካተት ለሚፈልጉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሩ ክፍት መሆኑን ግንባሩ አስታወቀ።

የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ  ግንባሩ አጋር ድርጅቶችን አካቶ በመዋሀድ አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ በጥቂት ወራት ውስጥ እንደሚመሠረት መግለጻቸው ይታወሳል።

ፋይል

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ባደረጉት ውይይት ‹‹ከጥቂት ወራት በኋላ የአፋር፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ የሶማሌ፣ የኦሮሞ፣ የአማራ ፓርቲ እያልን አንሄድም። እንደ ኢሕአዴግ ከጫፍ ጫፍ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በነፃነት የሚሳተፉበት አንድ አገራዊ ፓርቲ እንመሠርታለን፤›› ማለታቸው ይታወሳል።

በዚሁም በኢሕአዴግ ውሳኔ ብቻ የሚመረጥ የአገር መሪ የመሰየም አካሄድ እንደሚያበቃና የአጋር ድርጅቶች ሲያነሱ የቆዩት የፓለቲካ ውክልና ጥያቄም በዚህ እንደሚመለስ  ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሳዳት ነሻ የኢሕአዴግንና የአጋሮቹን ውህደት በተመለከተ የተከናወነው ጥናት መጠናቀቁን መግለጻቸውን ሪፖርተር ዘግቧል።

በጥናቱ የተለዩት ግኝቶችን መሠረት በማድረግ ሁሉም የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች በቅርቡ ከሚመሩት ማኅበረሰብ ጋር በተናጠል ውይይት ማድረግ እንደሚጀምሩም ነው የገለጹት።

ይሕ በእንዲህ እናደለም በኢሕአዴግና በአጋሮቹ ውህደት በሚመሰረተው አዲስ አገር አቀፍ ፓርቲ ውስጥ አባል ለመሆን የሚፈልጉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ካሉ መካተት እንደሚችሉ፣ ለዚህም ኢሕአዴግ በሩን ክፍት እንደሚያደርግ አቶ ሳዳት ገልጸዋል።

በሚመሠረተው አገር አቀፍ ፓርቲ ውስጥ አባል ለመሆን የሚፈልጉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ካሉ ማሟላት የሚጠበቅባቸው፣ የኢሕአዴግን መሠረታዊ ባህሪያት መቀበል ብቻ ነው ብለዋል።

ኢሕአዴግና አጋሮቹ የሚያደርጉት ውህደትም ነባር የኢሕአዴግ መሠረታዊ ባህርያትን ሳይለቅና እነዚህን መሠረታዊ ባህሪያትም ለሚመሠረተው አገር አቀፍ ፓርቲ በማውረስ የሚፈጸም መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

የብሔርና የቋንቋ ማንነቶች፣ እንዲሁም የፌዴራሊዝም ሥርዓት መርሆች ግን ተጠብቀው እንደሚቀጥሉ ኢህአዴግ አረጋግጧል።