ደቡብ ክልል ለዋልታ 19 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ፈቀደ

መስከረም ፳፬ ቀን ፳፻፮ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የደቡብ ክልል ብሔራዊ መንግስት መስተዳደር በክልሉ ያሉ ከተሞችን አስመልክቶ ዶክመንተሪ ፊልም ለማሰራት ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል 19 ሚሊዮን ብር ለመፍቀድ ስብሰባ መቀመጡን ምንጮች ለኢሳት ገለጹ፡፡

በፖለቲካ ውሳኔ ለመንግስታዊው ዋልታ የመረጃ ማዕከል ሊሰጥ የታቀደው ፕሮጀክት የደቡብ ክልል መገናኛ ብዙሀንን ቅር ማሰኘቱ ታውቋል፡፡

የክልሉ መገናኛ ብዙሀን በቂ መሳሪያና የሰው ሀይል እያለው ስራውን ግልጽነት በጎደለው ሁኔታ ለዋልታ እንዲሰጥ መወሰኑ ህገ-ወጥ አካሄድ መሆኑን እና ገዥው መንግስት የራሱ ድርጅቶችን ያልተገባ የመንግስት ገንዘብ እንዲጠቀሙ እያደረገ እንደሆነ ምንጮች አመልክተዋል፡፡

መንግስታዊው ዋልታ የመረጃ ማዕከል ለክልሉ መንግስት ሌላ ፕሮጀክት አስገብቶ እንዲፀድቅለት እየጠበቀ እንደሚገኝም ታውቋል፡፡

በደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ውስጥ እየተካሄዱ ያሉ አነስተኛና ጥቃቅን የንግድ ተቋማትን በዶክመንተሪ ፊልም ለመስራት ጥያቄ አቅርቦ ፓለቲካዊ ውሳኔ እንዲተላለፍ ዋልታ የመረጃ ማዕከል በመጠበቅ ላይ መሆኑን መረዳት ተችሏል፡፡

ከአምስት ዓመት በፊት የክልሉ መንግስት ዋልታ የመረጃ ማዕከል ‹ሀገሬ› የሚል ፕሮግራምን ለመስራት አስራ አንድ ሚሊዮን ብር ተፈቅዶለት እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የደቡብ ክልል በዘንድሮው የበጀት ዓመት ከፌደራል መንግስት ከተመደበለት 17 ቢሊዮን ብር ውስጥ በርካታ ገንዘብን ከፓለቲካ ጋር በተገናኙ ስራዎች እያባከነ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡