የህንድ ኩባንያ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይልን ሊያስተዳድር ነው

መስከረም ፳፬ ቀን ፳፻፮ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ኮርፖሬሽንን የሥራ ሂደት ለማስተዳደር አንድ የህንድ ኩባንያ ተመረጠ፡፡

ፖወር ግሪድ ኮርፖሬሽን ኦፍ ኢንድያ የተባለው ኩባንያ የኢትዮጵያን ኤሌክትሪክ ሀይል ለማስተዳደር የሁለት ዓመት ኮንትራት ተሰጥቶታል፡፡

መንግስት ድርጅቱን ለውጭ ኩባንያ መስጠት የወሰነው በድርጅቱ ውስጥ ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉና የተሻለ ስራን በሀገሪቱ ለማስተዋወቅ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር የሆኑት አቶ አለማየሁ ተገኑ ድርጅቱን ለውጭ ኩባንያ መስጠት የተፈለገው የአገልግሎት ተደራሽነትን በጥራት በግዜ እና በመጠን ከፍ ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ከፍተኛ የሆነ የኤሌክትሪክ ሀይል መቆራረጥ በመላ ሀገሪቱ ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ ዘንድሮ መታየቱን ሰሞኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ድርጅቱ በሀገሪቱ ያለውን ሀይል በበቂ ሁኔታ ማስተዳደር ባለመቻሉ የውጭ ኩባንያ በከፍተኛ ውጪ ድርጅቱን ለማስተዳደር መመረጡን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ተናግረዋል፡፡

ከህንድ ኩባንያ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ የኢትዮጵያ መንግስት 320 ሚሊዮን ብር ለሁለት ዓመት እንደከፈለ ታውቋል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ መንግስት የሀገሪቱን ቴሌኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤት ለማስተዳደር ለአንድ የፈረንሳይ ኩባንያ ለሁለት ዓመት በ600 ሚሊዮን ብር ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በድርጅቱ ውስጥ የታሰበው ለውጥ መምጣት ባለመቻሉ ኮንትራቱ እንዳይቀጥል ተደርጓል፡፡

የህንድ ኩባንያ  የኢትዮጵያ መብራት ሀይልን በሚያስተዳድርበት ወቅት ምንም የሰራተኛ ቅነሳ እንደማይኖር ቢያሳውቁም ሰራተኞች ግን ስጋት እንዳለባቸው በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

የፈረንሳይ ኩባንያ ቴሌኮሙኒኬሽን ባስተዳደረበት ወቅት ከ5 ሺህ በላይ ሰራተኞች ከስራቸው መፈናቀላቸው ይታወሳል፡፡