ህዳር 13 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ባለስልጣኑ በዋና ከተማዋ ኩዌት ሲቲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለኢሳት እንደተናገሩት፤ እየደረሰባት ያለውን ግፍ መቋቋም ሢሳናት ሰሞኑን አሰሪዋን ስለገደለችው ኢትዮጵያዊት ሴት ጉዳይ በመገናኛ ብዙሀን ከተሰማ ጀምሮ፤ ኢትዮጵያውያን በየ ቦታው እየተገደሉ ነው።
በዚህ ወር ብቻ እነሱ እንዳሉት ወደ ሰባት የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ኩዌት ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ተገድለዋል። ሁሉም በአሳዛኝና በሚያስደነግጥ ሁኔታ በየቦታው ሞተው መገኘታቸውን የጠቀሱት ኢትየጵያውያኑ፤ ይሁንና በ አገሪቱ ሚዲያዎች ስለ ሞታቸውም ሆነ ስለ አሙዋሙዋታቸው ምንም እንዳልተባለ ተናግረዋል።
ከነዚህም መካከል “አቦ ካሊፋ” እየተባለ በሚጠራው ስፍራ ተገድሎ፣ ሬሳው በስለት ተተልትሎ እና ተዘነጣጥሎ የተገኘው ኢትዮጵያዊው አብዱራህማን አንዱ ነው።
እንዲሁም በቅርቡ በቤት ሰራተኝነት ይተዳደሩ የነበሩ ሁለት ኢትዮጵያውያን ሴቶች በመኪና ተገጭተው መገደላቸውንም ኢትዮጵያውያኑ አመልክተዋል።
በጣም አሳዣኙና አሰቃቂው ግፍ ደግሞ… ኢትዮጵያውያኑ እንዳሉት ፦”ሃዋሊ አብን ሸራ ካልዱን” በተባለው ስፍራ ባለፈው እሁድ የተፈፀመው የጎዳና ትዕይንት ነው።
ምክንያቱ ምን እንደሆነ ማንም ምንም ባላለበት ሁኔታ አንድ ኩዌታዊ አሰሪ – የቤት ሰራተኛው የሆነችን አንዲት ወጣት ኢትዮጲያዊት ሴት፤ በጠራራ ጸሃይና ሰው በተሰበብሰበበት ጎዳና፤ መሬት ለመሬት እየጎተተ በመደብደብና በመቀጥቀጥ እዚያው ገድሏቷል-ኢትዮጵያውያኑ እያለቀሱ እንደተናገሩት።
ሰሞኑን ደግሞ በኩዌት ፦” ሲቲ ጃብር አሊ” እየተባለ የሚጠራው አካባቢ አንዲት ኢትዮጵያዊት የቤት ሰራተኛ ራስዋን እንዳጠፋች ተደርጎ በኩዌት ጋዜጣዎች መዘገቡን የጠቆሙት ኢትዮጵያውያኑ፤ ጋዜጣዎቹ እንደዛ ይበሉ እንጂ ስለ አሟሟቷ ምንም የተጣራ መረጃ አለመኖሩን ተናግረዋል።
በአሰሪዎችዋ ቤተሰቦች በሚደስርባት የረጅም ጊዜ ስቃይ በመነሳሳት የአሰሪዋን ልጅ ገድላለች የተባለችውና ካገር ልትወጣ ስትል በኩዌት አውሮፕላን ማረፊያ በፖሊስ መያዟ የተነገረው ኢትዮጵያዊቷ አይዳ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት እርምጃ እንደሚወሰድባት አረብ ታይምስን ጨምሮ በርካታ የኩዌት ሚዲያዎች እየዘገቡ ይገኛሉ።
ይሁንና ከአረብ ታይምስ ውጪ ያሉት ሌሎች የኩዌት ሚዲያዎች በ ኢትዮጵያውያኑ ላይ እየተፈፀመ ስላለው ግድያና ግፍ ምንም አለማለታቸው ታውቋል።
“በጭንቅ ውስጥ ነው ያለነው። ይሁ ሁሉ መከራ ሲደርስብን የሚረዳን ቀርቶ የሚያጽናናን አለገኘንም” የሚሉት ኢትዮጵያውያኑ፤በተለይ ኩዌት የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ያሳየው ዝምታ፤ እንዳሳዘናቸውና ልባቸውን እንዳደማው ይናገራሉ።
“ሰው በተለያየ ምክንያት ሊሞት ይችላል።በአደጋም፤በህመምም ህይወቱን ሊያጣ ይችላል። እዚህ በየቀኑ እየረገፉት ያሉት እህቶቻችን አሟሟት ግን እጅግ የከፋና ጭካኔ በተሞሉ ሰዎች የሚፈፀም ነው። ነገሩን ሊከታተልና ሊያጣራ የሚገባው ኤምባሲያችንም፤ ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ዝም ብሏል። ይልቁንም ሌላ ቢዝነስ ለመስራት እየተጣደፈ ይገኛል” ብለዋል-ኢትዮጵያውያኑ።
በኩዌት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሴቶች በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ የግድያ እና የመደፈር አደጋ እያጋጠማቸው እንደሚገኝ፤ ታዋቂው የአገሪቱ ጋዜጣ አረብ ታይምስ ባለፈው ወር በስፋት ዘግቧል።
ይሁንና መረጃው ወደ ሌሎች ዓለማቀፍ ሚዲያዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጆሮ በተገቢው ሁኔታ ደርሷል የሚል እምነት እንደሌላቸው የገለፁት ኢትዮጵያውያኑ፤ “ኤምባሲያችን ስንሞት ዝም ባለበት ሁኔታ ማን ሊደርስልን ይችላል? ከእንግዲህ ከአምላክ በታች ያላችሁን ተስፋ በምዕራቡ ዓለም የምትኖሩ ወንድምና እህቶቻችን ናችሁ። ስቃይና መከራችንን ለዓለማቀፉ ህብረተሰብ በማሰማት ህይወታችንን ትታደጉን ዘንድ አደራ እንላችሁዋለን” ሲሉ የድረሱልን ጥሪ አቅርበዋል።
በቅርቡ በፑንት ላንድ ሞት የተፈረደበት ኢትዮጵያዊው አስመሮም 700 ሺህ ብር ካልከፈለ ፍርዱ እንደሚፈፀምበት በተነገረው መሰረት፤ ቤተሰቦቹ ገንዘቡን ሰርተው እንደሚከፍሉ ቃል በመግባት መንግስት ብሩን በመክፈል ልጃቸውን እንዲታደግላቸው ቢማጸኑም፤ የጊዜ ገደቡ ሊጠናቀቅ አንድ ቀን እስኪቀረው ድረስ ከመንግስት ምላሽ ሊያገኙ ባለመቻላቸው፤ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) 700 ሺህ ብሩን በመክፈል ህይወቱን እንደታደገው መዘገቡ አይዘነጋም።
በሁኔታው ቁጭት ያደረበት ጋዜጠኛ ዓለማየሁ ገላጋይ በሰሞኑ ብዕሩ፦” የአንድ ኢትዮጵያዊ ዋጋ ስንት ነው?” ብሎ አጠንክሮ ጠይቋል።
ሰው ሰው አይሸትም በሚባለው በ አቶ መለስ መንግስት የልማት ፖሊሲ ግራ የተጋቡ ወገኖች፤ኢትዮጵያ፤ ግንብና ግድብ ለመስራት በሚል፤ ግንበኛውና ገዳቢው ችላ የተባሉባት አገር ናት ሲሉ ይደመጣሉ።