(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 20/2010) በግንቦት 20 ቀን የፖለቲካ እስረኞች የርሃብ አድማ ማድረጋቸው ተሰማ።
የርሃብ አድማውን ያደረጉት በቂሊንጦ እስር ቤት የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች መሆናቸውም ታውቋል።
እስረኞቹ የረሃብ አድማ ያደረጉት “ግንቦት 20 ለባርነት የተዳረግንበት ቀን ነው በሚል እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በአሁኑ ወቅት ከ250 በላይ እስረኞች በሽብር ስም ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት እየተከታተሉ ይገኛሉ።
እነዚሁም የፖለቲካ እስረኞች መሆናቸው ነው የተነገረው።
እስረኞቹ ከቂሊንጦ እስር ቤት የሚሰጣቸውን ምግብ “አንቀበልም” ብለው መመለሳቸው ታውቋል።
የፖለቲካ እስረኞች የርሃብ አድማ እያደረጉ ያሉት እየተሰቃየን ያለነው በግንቦት 20 ቀን ወደ ስልጣን በመጡ አምባገነኖች ነው “በሚል ምክንያት እንደሆነ ተነግሯል።
የ”ሽብር” ክስ ከተመሰረተባቸው እነዚህ እስረኞች መካከል አብዛኛዎቹ በቂሊንጦ የሚገኙ ናቸው ተብሏል።
እስረኞቹ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመብንም ነው ብለዋል።
መንግስት በሕዝብ አመጽ እና ግፊት በርካታ የፖለቲካ እስረኞችን መልቀቁ ይታወሳል።
ከነዚሁም መካክል አቶ አንዷአለም አራጌ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ ዶክተር መረራ ጉዲና እና ሌሎችም ይገኙበታል ።
በኢትዮጵያ በሕዝብ የሚታወቁና አለምአቀፉ ማህበረሰብ ድምጹን ያሰማላቸው እስረኞች ሲፈቱ አሁንም ግን በሺህዎች የሚቆጠሩ እስረኞች አሁንም በየእስርቤቱ ታጉረው ይገኛሉ።
ከመደበኛ እስር ቤቶች ውጭም ያሉበት የማይታወቅና በደህንነት ሃይሎች በርካታ ደብዛቸው የጠፉ ሰዎች እንዳሉም ይነገራል ።
በትግራይ ክልል ባዶ6 ተብሎ በሚታወቀው የማጎሪያ ስፍራም ከአማራ ክልል፣ ወልቃይትና ሌሎችም ስፍራዎች ታፍነው የተወሰዱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እስካሁን አለመፈታታቸው ይታወቃል።