ኢሕአዴግ የመሰነጣጠቅ እና የመከፋፈል አደጋ ይገጥመዋል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 20/2010) ኢሕአዴግ የመሰነጣጠቅ እና የመከፋፈል አደጋ እንደሚገጥመው የኢሕአዴግ የቀድሞ መሪዎች ገለጹ።

ትምክህተኛ እና ጠባብ የሚሉ ቃላትን መጠቀም ነውር  የሆነበት  አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ገብተናል ብለዋል።

የሕወሃት መስራች እና ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን ፣የሕወሃት  ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ እና ከብአዴን አቶ ሕላዊ  ዮሴፍ በመሩት የመቀሌው ስብሰባ በቅርቡ በጡረታ የተሰናበቱት  ዶክተር ካሱ ኢላላን ጨምሮ ጥቂት ነባር አባልትም ተሳታፊ ሆነዋል።

በመቀሌ በተካሄደው የግንቦት 20 ስብሰባ ላይ ከሕወሃቶች ጋር በመድረኩ ላይ የተገኙት የብአዴኑ የቀድሞ አመራር አባል አቶ ሕላዌ ዮሴፍ የኢሕአዴግ አስተሳሰብ መሸነፉን ‹‹የአስተሳሰብ ግንባታችንን ፌይል አድርጓል› ሲሉ ገለጸዋል።

ከ27 ዓመታት በፊት የተሸነፉ አስተሳሰቦች መልሰው አቆጥቁጠዋል ያሉት አቶ ህላዊ ዮሴፍ የመሬት ፖሊሲ እንዲሁም የብሄረሰብ መብት የመጣስ አዝማሚያ እያሳየ እንደሆነም አመልክተዋል።

“የሚፈለገውና የሚያስፈልገው ነገር ለትውልድ አልተላለፈም፤ አዲሱ አመራርም ይህንን አያውቅም፡፡” ሲሉ በመቀሌው የግንቦት 20 በዓል ላይ የተናገሩት አቶ ሕላዊ ዮሴፍ ትምክህተኛ እና ጠባብ የሚሉ ቃላትን መጠቀም ነውር የሆነበት  አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ገብተናል ብለዋል።

ኢህአዴግ የመሰነጣጠቅ እና የመከፋፈል አደጋ እንደሚገጥመውም አመልክተዋል።

የሕወሃት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው የቀድሞው ሥርዓት አስተሳሰብ አሁን በተለይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ  ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ እየተንጸባረቀ መሆኑን ገልጸዋል።

በሙስና የታሰሩ ሰዎች እንዴት ይፈታሉ በሚል ከተሰብሳቢው ለቀረበው ጥያቄ ምላሸ የሰጡት አቶ ስዩም መስፍን ከገንዘብ ሙስናው በላይ ዋናው ችግር  የአመለካከት ሙስናው ነው በማለት በሂደቱ እና በሕሊና እስረኞቹ መፈታት ቅሬታቸውን  አሳይተዋል ።

አቶ ስዩም  መስፍን አሁንም በሃገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ የትግራይ የበላይነት የለም በማለት ተከራክረዋል።

ከሰራዊቱ ውስጥ የትግራይ ተወላጆች ድርሻ 14 በመቶ ብቻ እንደሆነም ተናግረዋል።

ከፍተኛ ተቃውሞ ስለሚነሳበትና  በአመራሩ ውስጥ ስላለው የትግራይ ተወላጆች ድርሻ  ግን የጠቀሱት ነገር የለም።

በዚህ ስብሰባ በቅረቡ በጡረታ የተገለሉት ዶክተር ካሱ ኢላላ እና ሌሎች ጥቂት ነባር የኢሕአዴግ አመራሮች ተገኝተዋል።