(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 9/2010)
የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር የፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መኖሪያ ቤቶች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተሽጠው ለመንግስት ገቢ መሆናቸውን የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ አስታወቀ።
በእነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ መዝገብ ሕገ መንግስታዊ ስርአቱን በሃይል ለመናድ ሞክራችኋል በሚል በተመሰረተባቸው ክስ የሞት ፍርድ የተወሰነባቸው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ንብረታቸውም እንዲወረስ በፍርድ ቤት ተወስኗል።
ጠቅላይ አቃቢ ህግ አደረኩት ባለው የሃራጅ ሽያጭ የፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በጅምር ላይ ያለ መኖሪያ ቤት በ6 ሚሊየን ሶስት መቶ ሰማንያ ሺ ብር ተሽጦ ለመንግስት ገቢ መሆኑን አስታውቋል።
የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መኖሪያ ቤትም በአንድ ሚሊየን ብር ተሽጦ ለመንግስት ገቢ እንደሆነ ጠቅላይ አቃቢ ሕግ አስታውቋል።
ጠቅላይ አቃቢ ህግ በዚህም ሳይወሰን የፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የሆኑ የተለያዩ አክሲዮኖች፣ክሊኒክ፣ተሽከርካሪና ቴሌ ሴንተር ንብረቶችን በሐራጅ ለመሸጥና ገንዘቡን ለመንግስት ገቢ ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑንም በይፋ አስታውቋል።