የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣናቸውን ለቀቁ
(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 20/2009)የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋዝ ሸሪፍ የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሀላፊነታቸው ካገዳቸው በኋላ ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ።
ፍርድ ቤቱ የናዋዝ ሸሪፍን ስልጣን ያገደው ከሙስና ጋር በተያያዘ የቤተሰባቸውን ሀብት ካጣራ በኋላ ነው።
የፓናማ ሰነድ በመባል የሚታወቀውና የሙስና ወንጀሎችን ያጋለጠው የምርመራ ዘገባ የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋዝ ሸሪፍ ልጆች ከሀገር ውጭ ኩባንያ እንዳላቸው አጋልጦ ነበር።
ይህን ሰነድ ተከትሎም 5 አባላት ያሉት የፓኪስታን ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ ምርመራ እንዲደረግ ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር።
ናዋዝ ሸሪፍ የፓናማ ሰነድ በልጆቻቸውና በሃብታቸው ዙሪያ ያወጣውን ዘገባ ሲያስተባብሉ ቢቆዩም የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ግን ምርመራው ካለቀ በኋላ ከስልጣናቸው እንዲታገዱ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
ይህንኑ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ተከትሎ ታዲያ የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋዝ ሸሪፍ ስልጣናቸውን ለቀዋል።
የናዋዝ ሸሪፍ ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ይፋ እንዳደረገው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህግ ሂደቱ ላይ አስተያየት ለመስጠት ባይፈልጉም ስልጣናቸውን ግን በገዛ ፈቃዳቸው ትተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣኔን ለቅቄያለሁ በማለታቸውም በፓኪስታኗ ርእሰ ከተማ ኢስላማባድ ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ የመከላከያና የፖሊስ አባላት በኢስላማባድ ከተማ ተሰማርተዋል።
ከ5ቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች አንደኛው ሚስተር ናዋዝ ሸሪፍ ከእንግዲህ ታማኝ የሀገሪቱ የፓርላማ አባልና ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆኑ አይችሉም ሲል ተናግሯል።
ፍርድ ቤቱ በናዋዝ ሸሪፍ ላይ የሙስና ዶሴ እንዲከፈትና ክስ እንዲመሰረትባቸው ሃሳብ ማቅረቡንም የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
ክሱ ደግሞ የናዋዝ ሸሪፍ ልጅ ማርያምና ባለቤቷን ሰፍደር እንዲሁም የሀገሪቱን የገንዘብ ሚኒስተር ኢሻቅ ዳርና ሌሎችንም ይጨምራል ነው የተባለው።
የፓኪስታኑ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናስር አሊ ሳህን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ መነሻ በማድረግ ናዋዝ ሸሪፍ የፍትህ ሂደቱን በጸጋ እንዲቀበሉት ጥሪ አድርገዋል።