ታኀሳስ ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኮምሽኑ ያካሄደውና በይፋ ያልወጣው የጥናት ሰነድ እንደሚያመለክተው በኣለም ላይ ከእስያ ሀገራት ሲንጋፖር፣ሆንግ ኮንግ፣ ከአፍሪካ ቦስትዋናና ሞሪሺየስ በጸረ ሙስና ትግል በተጨባጭ ውጤታማ ከሆኑ ሀገራት መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸው አመልክቶ ፣ እነዚህ ሀገራት ለውጤት የበቁት የፖለቲካ አመራሩ ለጸረ ሙስና ትግሉ ቁርጠኛ በመሆኑና ራሱንም ከሙስና በማራቁ እንዲሁም ለሙስና ምርመራ ቢሮዎች የሰጠው ድጋፍና ነጻነት ከፍተኛ በመሆኑ ነው ይላል፡፡
በተጨማሪም የጸረ ሙስና ተቋማቱ በብቃታቸው የህዝብን ተአማኒነት ማግኘት መቻላቸው፣ ለሙስና የተጋለጡ የመንግስት አሰራሮች ተለይተው እንዲስተካከሉ መደረጋቸው፣ በጸረ ሙስና ትግሉ ሕዝቡን በስፋት ማሳተፍ በመቻላቸው፣ ለመንግስት ሠራተኛው የተለያዩ የማትጊያ መንገዶችን በመፍጠር ሙስናን የሚጠየፍ ዜጋ መፍጠር በመቻላቸው ለውጤት እንደበቁ ያትታል፡፡
በኢትዮጽያ የጸረ ሙስና ሕግ እና ሙስናን የሚከታተል ተቋም ቢደራጅም የፖለቲካ ቁርጠኝነት ባለመኖሩ በአጥፊዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ የላላ እንዲሆን አድርጎአል፡፡ በዚህ ምክንያት የሙስና ወንጀል እየረቀቀ እንዲመጣ በር ከፍቶአል፡፡
በጸረ ሙስና ትግሉ ውጤት ለማስመዝገብ የጸረ ሙስና ተቋም እንዲሁም የፖለቲካ ቁርጠኝነት መኖር ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ፣ በተጨማሪም ጠንካራ ዴሞክራሲ ተቋማት መኖር፣ ሙስናን የሚጠየፍና ሙሰኞችን የሚያገል ህብረተሰብ መፍጠር ለትግሉ ወሳኝ ነው ብሎአል፡፡
ከተጽዕኖዎች ነጻ የሆነና በገለልተኝነት የሚሰራ ተቋም የህዝብ አመኔታን ያተርፋል፣ ስራውም ውጤታማ ይሆናል ሲል ጥናቱ ምክረ ሀሳቡን ያቀርባል፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ መልካም አስተዳደርን ጨምሮ ሙስናና ብልሹ አሰራር ከከፍተኛ አመራሩን ጀምሮ መታየቱን በማመን ስርነቀል እርምጃ እንደሚወስድ ባለፈው ነሀሴ ወር በመቀሌ ጎባዔው የወሰነ ቢሆንም ፣ በተለይ በሙስና ወንጀል የሚጠረጠሩ ከፍተኛ የህወሃት አመራሮች ላይ እርምጃ ለመውሰድ እርስ በእርስ ፍርሃት በመንገሱ ችግሩን ወደታችኛው አመራር የመግፋት ዝንባሌ በማሳየት ላይ ነው።
በሌላ ዜና ደግሞ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ውስጥ ከፍተኛ ሙስና መፈጸሙን ዋና ኦዲተርን ጠቅሶ ሪፖርተር ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ዋና ኦዲተር ስራአስኪያጅ አቶ ገመቹ ዱቢሶ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ውስጥ በተጭበረበረ ሰነዶች ወጪ በማውጣት የሕዝብና የመንግስት ንብረትና ገንዘብ መመዝበሩን በፓርላማ ሪፖርታቸው አስታውቀዋል።
የኦዲት ድርጅቱ የደረሰበትን አጠቃላይ የሙስና ወጪዎች ያብራሩት አቶ ገመቹ በ2006 ዓ.ም. የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የበጀት አፈጻጸም ላይ ካቀረባቸው ከፍተኛ የሒሳብ ግኝቶች መካከል የመንግሥት ሕግና መመርያ ሳይፈቅድ ለሠራተኛ ማበረታቻ 198 ሽህ 783 ብር አላግባብ መክፈሉ፣ በህንድ አገር ለሚማሩ ሠራተኞች 124 ሽህ 264 ብርና ወደ ውጭ ለሥራና ሥልጠና ለሄዱ ሠራተኞች 18 ሽህ 444 ብር የኪስ አበል መክፈሉ በተጨማሪም ቢሾፍቱ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት በተዘጋጀ ሥልጠና ላይ ለሠልጣኞች የመኝታና የምግብ ወጪ ከተሸፈነ በኋላ ተጨማሪ 82 ሽህ 950 ብር በድምሩ 424 ሽህ 444 ብር አላግባብ መክፈሉ ታውቋል፡፡
ከፌዴራል መንግሥት የግዥ መመርያ ውጭ 1.4 ሚሊዮን ብር ከውል በላይ ለኤምኤች ኢንጅነሪንግ መክፈሉ እንዲሁም ከውል ውጭ 114 ሽህ 614 ብር ለዚሁ ድርጅት መክፈሉን ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም 742. ሚሊዮን ብር የምክር አገልግሎትና ግንባታ ግዥ ያለጨረታ መፈጸሙ በኦዲት መረጋገጡን ያስረዳል፡፡