ሚያዚያ ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የፌዴራል ዋና ኦዲተር በኢትዮጽያዊያን 2004 በጀት ዓመት በ116 የፌዴራል መንግስት ተቋማት ላይ ባካሄደው ኦዲት በድምሩ በ84 መ/ቤቶች ከ5 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ የጥሬ ገንዘብና የውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ በወቅቱ ያለመወራረድ ችግሮች ማግኘቱን ይፋ አደረገ፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር የ2004 በጀት ዓመት ሒሳብ የኦዲት ግኝት ሪፖርቱን ዛሬ ለፓርላማ ያቀረቡት ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ እንደተናገሩት የጥሬ ገንዘብ ሒሳብ አያያዝና ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ ፣በ3 መ/ቤቶች ብር 247,210.19 የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ተገኝቷል፡፡
በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ መጨረሻ በሂሳብ መግለጫ ሪፖርት የተደረገውና በቆጠራ የተገኘው ጥሬ ገንዘብ መካከል ልዩነት በ2 መ/ቤቶች ቆጠራው በብር 133,466.99 በማነስ እና በ9 መ/ቤቶች 3.4 ሚሊየን ብር በመብለጥ የታየ ሲሆን በአጠቃላይ በ24 መ/ቤቶች የተለያዩ የጥሬ ገንዘብና የባንክ ሂሳብ አያያዝ ድክመቶች መገኘታቸውን አጋልጧል፡፡
በሚኒስትሮች ም/ቤት የፋይናንስ አስተዳደር ደንብ ቁጥር 190/2002 አንቀጽ 32 አስከ 35 በተደነገገው መሰረት ተሰብሳቢ ሂሳብ በወቅቱ መወራረዱ ሲጣራ በ57 መ/ቤቶች ብር 1.4 ቢሊየን በደንቡ መሰረት በወቅቱ ሳይወራረድ ተገኝቷል፡፡ከዚህ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት የትምህርት ሚ/ር 401 ሚሊየን ብር፣የግብርና ሚ/ር 65 ሚሊየን፣የግብርና ቴክኒክና ሙያና ትምህርት ስልጠና ፕሮጀክት ማስተባበሪያ 156 ሚሊየን ብር፣የውጪ ጉዳይ ሚ/ር 174 ሚሊየን ብር፣የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ብር 160 ሚሊየን፣የሃገር መከላከያ ሚ/ር 87 ሚሊየን፣የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና የፈተናዎች ኤጀንሲ ብር 83 ሚሊየን ፣የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ 69 ሚሊየን፣የፌዴራል ፖሊስ 30 ሚሊየን ብር እና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ 21 ሚሊየን ብር ይገኙበታል፡፡
የግዥ አዋጅ፣ደንብና መመሪያን ሳይከተሉ የተፈጸሙ ግዥዎችን በተመለከተም በ30 መ/ቤቶች 354 ሚሊየን ብር ሕገወጥ ግዥ ተፈጽሞ ተገኝቷል፡፡ ከደንብና መመሪያ ውጪ ግዥ ከፈጸሙ መ/ቤቶች መካከል ጅማ ዩኒቨርሲቲ 240 ሚሊየን ብር፣የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ 36. ሚሊየን ብር፣ መቀሌ የኒቨርሲቲ 20. ሚሊየን ብር፣አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ14 ሚሊየን ብር፣ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ 9 ሚሊየን ብር፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ 7 ሚሊየን ብር ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን አቶ ገመቹ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ መ/ቤቶች የፈጸሙት ክፍያ ትክክለኛነቱ ለማጣራት ኦዲት ሲደረግ በ9 መ/ቤቶች በተለያየ ምክንያት ማስረጃ ባለመቅረቡ የወጪውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ያልተቻለ ሒሳብ ብር 3 ቢሊየን 500 ሚሊዮን ተገኝቷል፡፡ይህ ጥፋት ከተገኘባቸው መ/ቤቶች መካከል የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር 3 ቢሊየን 200 ሚሊየን ብር፣የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ብር 188 ሚሊየን፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ 41.ሚሊየን ብር፣ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ 30 ሚሊየን፣ ሰመራ ዩኒቨርሲቲ 14 ሚሊየን ዋናዋናዎቹ መሆናቸውን በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
ኦዲት በተደረጉ መ/ቤቶች ደንብና መመሪያን ጠብቆ ክፍያ በመፈጸም ሲጣራ በ21 መ/ቤቶች 137 ሚሊየን ከደንብና መመሪያ ውጪ ተከፍሎ ተገኝቷል፡፡
ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኦዲት ግኝቱ የሚታዩ ጉድለቶች እንዲስተካከሉ ለሚመለከታቸው መ/ቤቶች ማሳሰቢያ በየጊዜው የሚሰጥ ቢሆንም ችግሮቹ አሁንም አለመወገዳቸውን ለፓርላማው ገልጾአል፡፡ ከአመት አመት ማስተካከያ ይደረጋል እየተባለ በተደጋጋሚ ቃል ቢገባም መንግስት እርምጃ ለመውሰደ አልቻለም።