የፌዴራሉ አቃቤ ህግ በእነ ደሳለኝ እምቢአለ መዝገብ ስር ክስ በመሰረተባቸው አራት ተከሳሾች ላይ ምስክሮችን አሰምቶ ጨረሰ

ጥቅምት ፲፬ (አስራ ሶስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ መንግስት” የሽብርተኛ ቡድን ነው” ካለው ግንቦት ሰባት ድርጅት ጋር ግንኙነት ነበራቸው፤ አባል መልምለው አሰልጥነዋል፤ የሽብር ጥቃትም ለመሰንዘር ሲያሴሩ ነበር>> ሲል የፌዴራሉ አቃቤ ህግ በእነ ደሳለኝ እምቢአለ መዝገብ ስር ክስ በመሰረተባቸው አራት ተከሳሾች ላይ ከትላንት በስቲያ ስምንት ምስክሮችን አሰምቶ ጨረሰ።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት የአቃቤ ህግ ምስክሮችን የሰማው በሰኞ ዕለት ውሎው ነው።

 

በክስ ዝርዝሩ ላይም አንደኛ ተከሳሽ ደሳለኝ እምቢአለ ፤የፀረ -ሽብርተኝነት ህጉን በመጣስና የኢትዮጵያ መንግስት አሸባሪ ነው ባለው የግንቦት ሰባት ድርጅት ውስጥ አባል በመሆን፤ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ በድሉ ህንፃ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከሌሎች ግብረአበሮች ጋር በመሆን የግንቦት ሰባት የሲቪል ክንፍ የሆነውንና <<የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ጋርድ>> በመባል የሚታወቀውን ህቡዕ ድርጅት ለመመስረት ሢሰራ እና ለዚሁ ድርጅት የፕሮፓጋንዳ ሃላፊ ሆኖ ሲንቀሳቀስ ነበር >>ይላል።

<< ሁለተኛ ተከሳሽ አዳሙ ዘለቀ ደግሞ የግንቦት ሰባት ሲቪል ክንፍ በሆነው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ጋርድ ውስጥ አባል በመሆን፤ ከአንደኛ ተከሳሽ ጋር ለድርጅቱ አባል እንዴት መመልመል እንደሚቻል ለሶስት ቀናት ስልጠና ወስዷል>> ብሏል  የፌዴራል  አቃቤ ህግ።

 

እንዲሁም ፤በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ባምቢስ በሚባው አካባቢ አባል በመመልመልና የአመፅ ወረቀት በመበተን አመፅ የማስነሳት ተልዕኮ ለመፈፀም ተንቀሳቅሷል ይላል።

ሁለተኛው ተከሳሽ ከዚህም  በተጨማሪም የአመፅ ወረቀቱን በመበተን ለፈፀመው ተግባር ኡጋንዳ ከሚገኘውና ያረጋል (ሚኪ) ከሚባለው የግንቦት ሰባት አባል ድጋፍ እንደተደረገለት፤ በሪፖርት የተደገፈ ማስረጃ አግኝቻለሁ ሲልም ዐቃቤ ህግ ገልጿል።

 

ዜና 4-የአቃቤ ህግ ሶስተኛ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡት ስለሺ ጥጋቤ፤ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ውስጥ <መለስ >ከተባለው ሌላ አባል ጋር በመሆን ኮሎኔል አለበል አማረ ለሚመራው የድርጅቱ ወታደራዊ ክንፍ አባል የመመልመል ተልዕኮ ተቀብሏል የሚል ክስ ነው የቀረበባቸው።

አቃቤ ህግ አክሎም  ሦስተኛ ተከሳሽ ከዚህም ባሻገር ግንቦት 1 ቀን 2004 ዓ.ም ፋሲል የኔአለም ከተባለ የግንቦት ሰባት አመራር ጋር በስልክ በመገናኘት፤ ወቅቱ ለድርጅቱ ትግል ምቹ  ነው በሚል ሀሳብ አላማውን ለማስፈፀም ይንቀሳቀስ እንደነበር ያትታል።

ሦስተኛው ተከሳሽ ከዚህም በላይ በተለያዩ ቀናት ኤርትራ ከሚገኙ የግንቦት ሰባት አመራሮች ጋር በስልክ በመገናኘት ለሽብር ጥቃት ስልጠና ወደ ኤርትራ የሚሄዱ አባላትን ይመለምላል ሲልም ዐቃቤ ህግ ከሷል።

 

ሌላው በአቃቤ ህግ አራተኛ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡት  አቶ ተመስገን አበለ ናቸው።

ተከሳሽ የግንቦት ሰባት የሽብር ቡድን አባል በመሆን በህዳርና በታህሳስ ወር 2004 ዓ.ም በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ማርቆስ ከተማ ውስጥ በጊዜው ስሙ ካልታወቀ የአሸባሪ ድርጅት አመራር ጋር ለመገናኘት ለድርጅቱ አባል የመመልመል ተልዕኮን ተቀብሏል ሲል ዐቃቤ ህግ ወንጅሏል።

የፌዴራሉ ዐቃቤ ህግ  በማከልም፡_<<ተከሳሹ የግንቦት ሰባት የሽብር ቡድን አመራር አባል ከሆነው ፋሲል የኔአለም ጋር በመገናኘት ከሌሎች አገር ውስጥ ካሉ አባላት ጋር ስላደረገው ውይይትና ስለድርጅቱ የሀገር ውስጥ እንቅስቃሴ የገለፀ በመሆኑ፤ በሽብርተኛ ቡድን ውስጥ በመሳተፍ በፈፀመው ወንጀል ተከሷል >>ይላል።

ይሁንና አቃቤ ህግ ካቀረባቸው ምስክሮች መካከልም አንዳንዶቹ «ሰላማዊ የትግል መንገድ አክትሟል፤ አርበኞች ግንባርን መቀላቀል አለባችሁ» በሚል፤ መመልመላቸውን ነው  ለፍርድ ቤቱ ያስረዱት።

እንዲሁም ዐቃቤ ህግ በክሱ ላይ እንዳለው ተከሳሾቹ ከ ኮሎኔል አለበል እና ከፋሲል የኔ ዓለም ጋር ግንኙነት እንዳላቸው  የ ዓቃቤ ህግ ምስክሮች አለመስከራቸውን ሰንደቅ ዘገባ ያስረዳል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎትም አቃቤህግ ያቀረባቸውን ስምንት ምስክሮች ካደመጠ በኋላ ብይን ለመስጠት ለህዳር 4 ቀን 2005 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።