የቦዲ ብሄረሰብ አባላት 4 የፌደራል ፖሊስ አባላትን ገደሉ

ጥቅምት ፲፬ (አስራ ሶስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአካባቢው ምንጮች እንደተናገሩት የከባድ መኪና ሾፌሮች 6 የቦዲ አባላትን በመግጨታቸው እና ቦዲዮች በወሰዱት እርምጃ 7 ሲቪሎችንና 4 የፌደራል ፖሊስ አባላትን ገድለዋል።

በአካባቢው ከሚካሄደው የስኳር ልማት ጋር በተያያዘ በበቦዲና በመንግስት መካከል አለመግባባት እንዳለ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።

በአሁኑ ጊዜ ውጥረቱ በመጨመሩ በሁለት የፌደራል ፖሊስ ኦራል መኪና የተጫኑ ልዩ ሀይል ወደ አካባቢው አቅንቷል። የክልሉ ፖሊስ አባላትም ወደ አካባቢው መሰማራታቸው ይታወቃል።

ዜና 3

የልማት ጥያቄ ያነሱ  ወጣቶች 3 አመት ተፈረደባቸው

ጥቅምት ፲፬ (አስራ ሶስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በደቡብ ኦሞ በጅንካ ከተማ የሚሰራውን የአስፓልት መንገድ መጓተት የተቃወሙና ሌሎችንም የልማት ጥያቄዎችን ያነሱ በርካታ ወጣቶች ያለ ማስረጃ በአስተዳዳሪው ትእዛዝ ብቻ 3 አመት እንዲታሰሩ መደረጉን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ኢሳት ከወር በፊት የወጣቶችን መታሰር መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን ፣ የወረዳው ፍርድ ቤት ወጣቶቹ የጠየቁት የልማት ጥያቄ በመሆኑ እንደማያስከስሳቸው ውሳኔ አስተላልፎ ነበር። ይሁን እንጅ የወረዳው አስተዳዳሪ ለወረዳው ዳኛ በሰጡት ጥብቅ ትእዛዝ ወጣቶቹ እንዲታሰሩ ተደርጓል።

በከተማው የአስፓልት ስራ እንዲሰራ ኮንትራት የተዋዋለው ግለሰብ ” አስፓልቱን ቶሎ እንዲያጠናቅቅ ከህዝቡ ጥያቄ ቢቀርብለትም” ” “እኔ ከመለስ ጋር አብሬ የታገልኩ ነኝ፣ ምንም አታመጡም” የሚል መልስ መስጠቱን ነዋሪዎች ገልጠዋል።

በአካባቢው ስላለው ከፍተኛ ችግር በተደጋጋሚ ስንዘግብ መቆየታችን ይታወቃል።  በዚሁ ዙሪያ የወረዳውን ባለስልጣናት ለማግኘት በተደጋጋሚ ብንሞክርም አልተሳካልንም።