(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 21/2011)የፌደራል ፖሊስ በሌሉበት ጉዳየቸው እየታየ ያለው እነ አቶ ጌታቸው አሰፋ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የተሰጠው የመጥሪያ ትዕዛዝ በጊዜ ከፍርድ ቤት ባለመውጣቱ ማድረስ አልቻልኩም ሲል ገለፀ።
የፌደራል ፖሊስ ትዕዛዙ የተሰጠው ግንቦት ስምንት ቢሆንም የመጥሪያ ትዕዛዙ ከፍርድ ቤት የወጣው ግንቦት 14 በመሆኑ ትግራይ ክልል ድረስ ሄዶ ለተከሳሾች ለማድረስ የጊዜ ዕጥረት አጋጥሞኛል ብሏል።
የቀድሞው የደህንነት ሐላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ የተከሰሱ ሰዎች ችሎት እንዲቀርቡና መጥሪያ እንዲደርሳቸው ፍርድ ቤት አዞ ነበር።
የፌዴራል ፖሊስ ግን ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የተሰጠውን ትዕዛዝ እስካሁን አላደረሰም።
ፌዴራል ፖሊስ ለዚህ የሰጠው ምክንያትም የመጥሪያ ትዕዛዙ ከፍርድ ቤት ሳይወጣ ስልዘገየብኝ ነው ብሏል።
እንደ ፌዴራል ፖሊስ ገለጻ ትዕዛዙ በፍርድ ቤት የተሰጠው ግንቦት ስምንት ቢሆንም የመጥሪያ ትዕዛዙ ከፍርድ ቤት የወጣው ግንቦት 14/2011 ዓም ነው።
እናም ትዕዛዙን ተግባራዊ ለማድረግ ፌደራል ፖሊስ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል ።
ፍርድቤቱም የፖሊስን ጥያቄ ተቀብሎ ለሰኔ 3 ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱን ዘገባዎች አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ለምስክርነት ያቀረበውን የሲዲ ማስረጃ ለተከሳሾች እንዲያደርስ በፍርድ ቤቱ የተሰጠውን ትዕዛዝ ከአንድ ሲዲ በስተቀር ሁሉንም በማድረስ ተግባራዊ ማድረጉን ገልጿል።
አቃቢ ህግ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ምስክርነት እየሰጡ ያሉ አካላት ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ማንነታቸው ሳይታወቅ ምስክርነት እንዲሰጡ ይፈቀድለት ዘንድ የምስክርነትና የወንጀል ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ 690/2003 በመጥቀስ ጠይቋል።
ፍርድቤቱ በዚህ ጉዳይ ላይም ውሳኔ ለመስጠት ለሰኔ 3 ቀጠሮ ሰጥቷል።
እንደ ኢቢሲ ዘገባ ተከሳሾች በበኩላቸው ደሞዛቸው በመቆሙ ቤተሰቦቻቸው ለችግር መጋለጣቸውን ጠቅሰው ለፍርድቤቱ አቤቱታ አቅርበዋል።
ጉዳዩን እየተከታተለ ያለው የፌዴራል ከፍተኛ ደረጃ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ግን ይህ ፍርድ ቤት ደሞዝ ክፈል አትክፈል የማለት ህጋዊ መሰረት ስለሌው ለሲቪል ሰርቪስ ወይም ለሚመለከተው አካል ማመልከት ትችለላችሁ ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል።