ማህበረ ግዮራን ዘረኢትዮጵያ ዘጠኝ ኢትዮጵያዊያን ሴቶችን ሊሸልም ነው

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 16/2011)ሲድ የተባለው በአሜሪካ የሚገኝ የሽልማት ድርጅት ዘጠኝ ኢትዮጵያዊያን ሴቶችን በክብር ሊሸልም መሆኑን አስታወቀ።

ማህበረ ግዮራን ዘረኢትዮጵያ (ሲድ) ተብሎ የሚታወቀው ተቋም ለወደፊት ተስፋ የተጣላባቸውን ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ይሸልማል።

ከተሸላሚ ሴቶች መካከል የጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ማአዛ አሸናፊ፥አትሌት ኮለኔል ደራርቱ ቱሉ እና ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሴም ይገኙበታል።

የማህበር ግዮራን ዘረ ኢትዮጵያ(ሲድ) 27ኛ አመት የክብር ሽልማት የሚካሄደው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ግንቦት 26/2019 ዓ.ም ነው።

ሽልማቱ ሜሪላንድ በሚገኘው ኮሌጅ ፓርክ ማሪዮት ሆቴል ሲካሄድም በልዩ ልዩ የሙያ ዘርፎች የላቀ ደረጃ የደረሱና በስራቸው ሀገርን ላኮሩ ዘጠኝ ኢትዮጵያውያን ሴቶች የክብር ሽልማት እንደሚሰጣቸው ታውቋል።

የዘንድሮው የሲድ ተሸላሚ ሴቶች የሽልማት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ ፣ ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ ፣ ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሴ ፣ ዶክተር ሰናይት ፍሰሀ ፣ ካፒቴን አምሳለ ጓሉ፣ አርቲስት ጁሊ ምህረቱ፣ ዶክተር አለምጸሃይ መኮንን ፣ ወይዘሮ ሔለን መስፍን፣ ወይዘሮ ልደት ሙለታ ናቸው።

ከነዚህም የክብር ተሸላሚ ሴቶች በተጨማሪም በትምህርታቸው እጅግ አመርቂ ውጤት ያገኙና ለወደፊት ተስፋ የተጣለባቸው ወጣቶች ማለትም ኤደን ፍስሀ፣ ቤዛዊት ጋሻ፣ ቃልኪዳን ሃይሌ፣ ማያ ከበደ፣ መቅደስ ሽፈራው እና ገብርኤል ሲራክን ይሸልማል።

በእለቱ ልዩ እራት የተዘጋጀ ሲሆን ተሸላሚዎችን  የማክበር ስነስርአት ፣ የፓናል ውይይት ፣ስነግጥም፣ ስነስዕልና የሙዚቃ ዝግጅቶች እንዳለም ሲድ ያወጣው መግለጫ አመልክቷል።