ሰኔ ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የፊታችን እሁድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከደቡብ አፍሪካው ብሔራዊ ቡድን ጋር በአዲስአበባ
ስታዲየም የሚያካሂደው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ወሳኝ ግጥሚያን በመሃል ዳኝነት የሚመሩት ግብጻዊ ዳኛ በመሆናቸው
ጨዋታው በሰላም የመጠናቀቁ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ስጋት አሳድሯል።
ኢትዮጵያ እያስገነባችው ያለችው የአባይ ግድብ አቅጣጫውን እንዲቀይር መደረጉን ተከትሎ በግብጽ ከተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ግብጻዊው ዳኛ በአዲስአበባ ስታዲየም ዛቻ፣ ስድብና አካላዊ ትንኮሳ ሊፈጸምባቸው የሚችል ከሆነ ድርጊቱ ለኢትዮጽያ አደገኛ መሆኑን የስፖርት ባለሙያዎች ግልጸዋል፡፡ ግብጻዊው ዳኛ አንዳች ኣይነት ጥቃት የሚፈጸምባቸው ከሆነ ኢትዮጵያን በማሸነፍ
ወይም አቻ በመውጣት ነጥብ ካልተጋራ በስተቀር የማለፍ ዕድል ለሌለው የደቡብ አፍሪካ ቡድን መልካም አጋጣሚ
ሊፈጠርለት እንደሚችል ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ ባለሙያ ለአዲስ አበባው የኢሳት ዘጋቢ ገልጸዋል፡፡
የእሁዱ ጨዋታ በረብሻ ምክንያት ቢስተጓጎል የደቡብ አፍሪካ ቡድን በፎርፌ በቀጥታ የሚያልፍ ከመሆኑም በላይ ድርጊቱ በኢትዮጽያ ላይ ከበድ ያለ ቅጣትን ሊያስከትል ይችላል።
ከአንድ ዓመት በኋላ ብራዚል በምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፉ ቡድኖችን ለመለየት እየተካሄደ ባለው
የማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ሁለት ጨዋታዎች እየቀሩዋት አስር ነጥብን በመያዝ ምድቧን እየመራች ትገኛለች፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የእሁዱን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ ከምድቡ የበላይነትን የማግኘቱ ጉዳይ የተረጋገጠ
ይሆናል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን ከኢትዮጽያ ጋር በሜዳው ከዚህ በፊት ባካሄደው ጨዋታ አንድ እኩል
መለያየቱ አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል፡፡