የጸጥታና የደህንነት ተቋማት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ሆነው እንዲሰሩ ይደረጋል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 8/2010)የኢትዮጵያ የጸጥታና የደህንነት ተቋማት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ሆነው እንዲሰሩ ይደረጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ተናገሩ።

ለቅሬታ ምንጭ የሆኑ ሕጎችም ማሻሻያ እንደሚደረግባቸው ቃል ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ይህንን የተናገሩት ትላንት በሚሊኒየም አዳራሽ በተጠራ ሕዝባዊ መድረክ ላይ መሆኑም ታውቋል።

ከጅጅጋና አምቦ ፣ በቤተ መንግስት ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና  ከመቀሌ በኋላ በተካሄደው  የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አምስተኛው የሚሊኔም አዳራሽ መርሃግብር  በርካታ ጉዳዮችን የዳሰሱ ሲሆን የሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ችግር ያለበትንም አሳሳቢ ሁኔታ ተመልክተዋል።ለመፍትሔው መንግስትም ኣንደሚንቀሳቀስና ሕዝቡም ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በትምህርት ጥራት ረገድ ያለውንም ችግር የዳሰሱት ዶክተር አብይ አሕመድ በዚህም ዙሪያ የትምህር ጥራትን ለማስጠበቅ መንግስታቸው እንደሚንቀሳቀስ ቃል ገብተዋል።

ቀጣዩ ምርጫ ፍትሃዊና ነጻ እንዲሆን እንዲሁም ተቃዋሚ ሃይሎች እንዲጠናከሩ ስራዎች ይሰራሉ ሲሉም ተናግረዋል።

የጸጥታና የደህንነት ተቋማት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ሆነው እንዲሰሩ ይደረጋል በማለትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የመከላከያ ሰራዊቱና የደህንነት መዋቅሩ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ እንዲሆን ይደርጋል  ማለታቸውን የተከታተሉ የፖለቲካ ተመልካቾች  ትልቅ ርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።ሆኖም ከፖለቲካ ወገንተኝነት በላይ በአንድ ብሔረሰብ ተወላጆች የተያዘው የሀገሪቱ ወታደራዊ አመራር ላይስ ምን  አይነት ማስተካከያ ይደረጋል ሲሉም የፖለቲካ ተመልካጮቹ  ይጠይቃሉ።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ስለቀጣዩ ምርጫ የተናገሩትንም የሚተቹ የፖለቲካ ምሁራን የሀገሪቱን ችግር ውስብስብነት በማጤን ለሁሉን አቀፍ ጉባኤና ለሽግግር ሒደት ሁኔታዎችን ቢያመቻቹ ይበጃል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰተዋል።