የጣሊያን መንግስት ስደተኞችን የጫኑ ሁለት መርከቦችን አገደ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 15/2010) የጣሊያን መንግስት ስደተኞችን የጫኑ ሁለት መርከቦችን በህገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ አግኝቻቸዋለሁ በሚል ማገዱን አስታወቀ።

የጣሊያን መንግስት አግቻቸዋለሁ ያላቸው መርከቦች 226 ከአዳጋ የተረፉ ስደተኞችን ጭነው እንደነበርም ታውቋል።

ከሊቢያ ወደብ የተነሱትንና አደጋ ላይ ወድቀው የነበሩትን ስደተኞች የጫኑት መርከቦች የሆላንድን ባንዲራ ሲያውለበልቡ እንደነበርም መረጃው አመልክቷል።

በጣሊያን በቅርብ አዲስ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር መመረጣቸውን ተከትሎ  የሜዲትራኒያንን በባህር አቋርጠው የሚመጡ ስደተኞችን ሃገሪቱ አልቀበልም ማለቷን ሰሞኑን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡት ቆይተዋል።

በቅርቡ በነብስ አድን ሰራተኞች ከአደጋ የተረፉ 629 ስደተኞችን በሩዋን ዘግታ አልቀበልም ማለቷንም በማሳያነት ያቀርባሉ።

አሁን ላይ ደግሞ የነብስ አድን ስራ የሚሰሩና በውስጣቸው 226 ስደተኞችን የጫኑ መርካቦችን ማገዷ ተሰምቷል።

ምክንያት አድርጋ ያስቀመጠችውም መርከቦቹ በድንበሬ ዙሪያ የሆላንድን ባንዲራ እያውለበለቡ በህገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ አግኝቻቸዋለሁ የሚል ነው።

በጣሊያን በኩል እግድ የተጣለባቸውና የጀርመን የነፍስ አድን ሰራተኞችን የጫኑት መርከቦች ግን ሆላንድ ውስጥ ያልተመዘገቡ መሆናቸውንና የሆላንድን ባንዲራም ሲያውለበልቡ አለመታየታቸውን ገልጸዋል ሲል ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮን የጣሊያን መንግስት የወሰደው ርምጃ ፈጽሞ ሀላፊነት የጎደለው ድርጊት ነው ማለታቸው ተሰምቷል።

የጣሊያኑ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው እኛ ምናልባት ስደተኞችን ጠልታችኋል በሚል ልንፈረጅ እንችላለን።

ነገር ግን በራቸውን ከፍተው ስደተኞችን ከተቀበሉ ሀገራት በቂ ትምህርት ወስደናል ማለታቸው ተሰምቷል።የወሰዱት ትምህርት ምን እንደሆነ በግልጽ ባያስቀምጡትም እንኳ።

የአውሮፓ ህብረት ሀገራት ስደተኞቹን በተመለከተ በብራስልስ ለመምከር ቀጠሮ መያዛቸው የተሰማ ሲሆን ጣሊያን በበኩሏ የኔን ጥቅም የሚያስቀድም ካልሆነ ምንም አይነት ውሳኔ ቢያስተላልፉ አልስማማም ማለቷን ቢቢሲ ዘግቧል።

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ቢሮ እንዳወጣው መረጃ ከሆነ በቅርቡ ብቻ 222 ስደተኞች ሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ ሰጥመው ሕይወታቸውን አጥተዋል።