የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንቱ ስራ የሚ ለቁ ዳኞች ቁጥር መጨመሩን ተናገሩ

ሰኔ ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ተገኔ ኔታነህ ሰሞኑን ለፓርላማ የመ/ቤታቸውን የ11 ወራት ሪፖርት
ባቀረቡበት ወቅት  ዳኞች በርካታ ችግሮች የተጋረጠባቸው በመሆኑ መስሪያቤቱን እየለቀቁ ነው ብለዋል።

የዳኞች መኖሪያ ቤት ችግርን በዘለቄታነት ለመፍታት ሕንጻ ለመገንባት እየተደረገ ያለው ጥረት የተወሰነ መጓተት እንደሚታይበት ፕሬዚዳንቱ ጠቁመው እስከዚያ ድረስ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ መንግስት የኪራይ ቤት መስጠቱን እንዲቀጥል የተላለፈውን ውሳኔ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ተግባራዊ ባለማድረጉ ችግሩ ቀድሞ ከነበረበት ተባብሶ መቀጠሉን ፕሬዚዳንቱ  ገልጸዋል፡፡
የዳኞች እጥረትንም በተመለከተ አቶ ተገኔ ሲያስረዱ በዚህ ዓመት 58 ያህል ዳኞች በመሾማቸው የነበረውን የዳኞች
እጥረት በመጠኑም ቢሆን ለመቅረፍ የተቻለ ሲሆን ነገር ግን ቀደም ሲል በርካታ ዳኞች ፍ/ቤቶቹን የለቀቁ
በመሆናቸው ካለው ፍላጎት አንጻር በቂ ሆኖ አልተገኘም ብለዋል፡፡

በተለይ በድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች በኩል እያጋጠመ ያለው ፍልሰት ከፍተኛ ችግር መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ ብዙዎቹ ሰራተኞች ስራ የሚለቁት በሚሄዱበት መ/ቤት የተሻለ ደመወዝና ጥቅማጥቅም በተለይም የሰርቪስና ሌሎች አገልግሎቶች በማግኘታቸው ነው ያሉት አቶ ጌታነህ በለቀቁ ሰራተኞች ምትክ ሰራተኛ ለመቅጠር የሚደረገው ሙከራ አብዛኛውን ጊዜ አይሳካም ሲሉ ምሬታቸውን ለፓርላማው
አስረድተዋል፡፡

ብዙዎቹ በክፍት ቦታዎች በሚወጡ ማስታወቂያዎች መሰረት ተወዳድረው ማሸነፋቸው ከተገለጸላቸውና የሐኪም ማስረጃ እንዲያቀርቡ ከተነገራቸው በኋላ በዚያው ነው የሚቀሩት ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በማስቻያ ቦታና በቢሮ ጥበት በኩል ያለው ችግር አሁንም አለመቃለሉን ጠቅሰው እንደ አብነት የፌዴራል ከፍተኛው ፍ/ቤትን አንስተዋል፡፡ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 33 ችሎቶች ተቋቁመው አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን ለነዚህ ችሎቶች መጠቀሚያ የሚያገለግሉ 15 የማስቻያ አዳራሾች ብቻ ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ችሎቶች በፈረቃ ለመስራት ተገደዋል፡፡ ይህም ዳኞችን በሙሉ አቅማቸው እንዳይሰሩ ከማድረጉም በላይ ባለጉዳዮች እየተጉላሉ ነው ሲሉ
በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡
ፍ/ቤቶች የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ፣መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ለልማትና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ
እየተደረገ ባለው ጥረት ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ ችግሮቻቸው ሊቀረፉላቸው እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡

ብዙ ዳኞች በፖለቲካ ተጽኖ የተነሳ ስራቸውን በነጻነት ለመስራት ባለመቻላቸው ስራቸውን እንደሚለቁ የተለያዩ ጥናቶች ቢያመለክቱም፣ የፖለቲካውን ችግር ፕሬዚዳንቱ በሪፖርታቸው አላከተቱም። ኢትዮጵያ ውስጥ ነጻ የሆነ የፍትህ ስርአት አለመኖሩን በቅርቡ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ባወጣው አመታዊ ሪፖርት ላይ ተመልክቷል።