የግብርና ኢንቨስትመንትን የሚመራ ኤጀንሲ በመቋቋም ላይ ነው

ሰኔ ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-የኢትዮጽያ መንግስት የግብርናውን ኢንቨስትመንት የሚያደራጅና የሚመራ የግብርና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ በማቋቋም
ላይ መሆኑ ተሰማ፡፡
አቶ ወንድይራድ ማንደፍሮ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ከመንግስት መገናኛ ብዙሃን ጋር ሰሞኑን ባደረጉት ቃለምልልስ
በመንግስት በኩል የግብርናን ኢንቨስትመንት በማጠናከር ሰፋፊ የግብርና ልማቶች በአገሪቱ እንዲኖሩ መንግስት
ፍላጎት እንዳለው በመጥቀስ ይህን የማጠናከር ስራ ለማከናወን አደረጃጀቱ እንዲስተካከል መደረጉን ገልጸዋል፡፡
የኤጀንሲው ማቋቋሚያ በሚኒስትሮች ም/ቤት መጽደቁን፣ ኤጀንሲው በተለይ ሰፋፊ መሬቶች ባሉባቸው ክልሎች የራሱ
ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እንደሚኖሩት፣ የተጠናከረ ባለሃብቶችን የሚደግፍ አመራር እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በግብርና ኢንቨስትመንት 5 ሺ 200 ያህል ባለሃብቶች መኖራቸውን ቀደም ሲል መሬት በክልሎች ይሰጥ
የነበረው በአሁኑ ወቅት በፌዴራል መንግስት ወጥነት ባለው አሰራር እንዲከናወን መደረጉን፣የፌዴራል መንግስት
ስራውን ከያዘው በኋላ ወደዘርፉ የገቡ ባለሃብቶች ቁጥር ከ15 እንደማይበልጥ አስረድተዋል፡፡

አብዛኛው የግብርና ኢንቨስትመንት በኢትዮጽያዊያን መያዙን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው እስካሁን የውጪ ባለሃብቶች ቁጥር 250 ብቻ ነው ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል ለሚያለሙትም ለማያለሙትም ባለሃብቶች ሰፋፊ መሬቶች የተሰጡበት ሁኔታ እንደነበር የጠቆሙት አቶ
ወንድራይድ ባለፉት ሁለት ዓመታት ይህን ችግር በማስተካከል ከሶስት ሺ ሄክታር ያልበለጠ መሬት ሲሰጥ መቆየቱን
ገልጸዋል፡፡
“የእኛ መርህ አንድ ባለሃብት እስከ አምስት ዓመት ድረስ ሊያለማ የሚችለውን መሬት እንዲሰጠው ነው፡፡ ይህን ካለማ
በኋላ ማስፋፊያ መጠየቅ ይችላል፡፡ ምክንያቱም አምስት ዓመት ድረስ መጠበቅ እንችላለን፤ከአምስት ዓመት በኋላ ግን
ካላለማ መሬቱን ይነጠቃል” ብለዋል ባለስልጣኑ፡፡ አሁን በወጣው መመሪያ መሰረት ለጀማሪ ባለሃብት የሚሰጠው መሬት
ከ10 ሺ ሄክታር በላይ እንደማይበልጥም አክለዋል፡፡ ባለሃብቱ ከግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ጋር የመጣ ከሆነ
ሊጨመርለት እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡
ሰፋፊ እርሻዎችን ለማስፋፋት በመንግስት በኩል አሰራሩ ፍጥነት የሌለው መሆኑን የተቹት ሚኒስትር ዴኤታው በአማካይ
በዓመት ለባለሃብቶች መዘጋጀት የቻለው መሬት እስከአንድ ሺ ሄክታር ነው ብለዋል፡፡
“እስካሁን ወደ ግብርና ልማት የገቡ ባለሃብቶች ማበርከት የሚገባቸውን ያህል እያበረከቱ ነው ወይ?” በሚል
ለቀረበላቸው ጥያቄ “የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም እያበረከቱ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ሰፋፊ በተለይ እንደ ህንድ ላሉ ባለሃብቶች ገበሬዎችን በማፈናቀል  የእርሻ መሬቶችን
መስጠቱ የመሬት መቀራመት ነው በሚል ሰፊ ትችቶች ሲቀርቡበት መቆየቱ አይዘነጋም፡፡ መንግስት እስከ 4 ሚሊዮን ሄክታር የሚደርስ መሬት ለውጭ ባለሀብቶች ለመስጠት መዘጋጀቱን በተደጋጋሚ ገልጿል። እንደ ኦክላንድ ኢንስቲቲዩት የመሳሰሉ ታዋቂ ተቋማት በኢትዮጵያ የሚታየውን የመሬት መቀራመት በተደጋጋሚ ሲቃወሙ ቆይተዋል። መንግስት ያለ በቂ ጥናት በነጻ በሚባል ዋጋ የሰጣቸውን መሬቶች መልሶ ለመውሰድ ወይም አዲስ የኮንትራት ውል ለማስፈረም እቅድ ይኑረው አይኑረው የታወቀ ነገር የለም ።

በተመሳሳይ ዜና ደግሞ የአሜሪካ የልማት ተራድኦና የኢትዮጵያ የግብርና ሚኒስቴር በጋራ በኢትዮጵያ ያለውን የመሬት አስተዳደር፣ የይዞታ ሁኔታ እና የማህበረሰብ መሬቶችን በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል አዲስ መርሀግብር በነገው እለት ይፋ ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ የግብርና ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ስለሺ ጌታሁን እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በጋራ መርሀግብሩን ይፋ እንደሚያደርጉ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።