የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን የለውጥ ጅምር ለማወደስ የሀረር ሕዝብ ለነገ የድጋፍ ሰልፍ ለማድረግ ያቀረበው ጥያቄ በመስተዳድሩ ሳይፈቀድ ቢቀርም ሕዝቡ የፊታችን ቅዳሜ በራሱ ኃላፊነት ሰልፍ ለመውጣት መዘጋጀቱ ተገለጸ።
(ኢሳት ዜና ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ/ም) የሀረር ነዋሪዎች በተለይ ለኢሳት እንደገለጹት የሀረር ከተማን ጨምሮ በወረዳው ከተሞችና ገጠሮች በሙሉ ጅምር ለውጡን የሚያወድስ የድጋፍ ሰልፍ ለማድረግ ሕዝቡ ቢጠይቅም፣ የክልሉ መስተዳድር “ በሰልፎቹ የጸጥታ ችግር ሊከሰት ስለሚችል፣ ለዚያ ኃላፊነትን አልወስድም “በማለት የፈቃድ ጥያቄውን ሳይቀበላቸው ቀርቷል።
ሌሊች ክልሎች ተመሣሳይ ፈቃዶችን በአግባቡ ሲያስተናግዱ የሀረሪ ክልል – “የአካባቢውን ጸጥታ መቆጣጠር አልችልም” በሚል ምክንያት የድጋፍ ሰልፉን መከልከሉ እንዳሳዘናቸው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
በርካታ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የነሱብኛል ብሎ የሚሰጋው የሀረሪ ክልል ሰልፉ እንዲካሄድ ፍላጎቱ እንደሌለው ተረድተናል ያሉት አስተባባሪዎቹ፣ የጻፍነው ደብዳቤ ፕሬዚዳንቱ ጋር ቢደርስም የሕዝቡን ፍላጎት ሊያስተናግዱ አልፈቀዱም ብለዋል።
ይሁንና በመስተዳድሩ አሉታዊ ምላሽ ሳቢያ የነገው ሰልፍ ቢደናቀፍም የፊታችን ቅዳሜ ሰኔ ፴ ቀን በሁሉም የወረዳው ከተማዎችና ገጠሮች የሞኖረው ሕዝብ በራሱ ፈቃድና ኃላፊነት ሰልፍ እንደሚወጣ ያሳወቁት ቄሮዎች፣ በሰልፎቹ ላይ አንድም የታጠቀ መከላከያም ሆነ ፖሊስ እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።
“ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተፈጸመው የቦምብ ጥቃት አኳያ ለሰልፎቹ ደህንነት ሲባል የጸጥታ ሠራተኞች ቢመደቡላችሁ የተሻለ አይሆንም ወይ፧” በማለት ኢሳት ላቀረበላቸው ጥያቄ አስተባባሪዎቹ በሰጡት ምላሽ፦ “ጸጥጣ በማስከበርና በተመሣሳይ የደህንነት ጥንቃቄዎች ዙሪያ ቄሮ ሙሉ ኃላፊነቱን ይወስዳል።ታጣቂዎቹን አንፈልግም። እንደውም በነሱ ሽፋን ነው ጥቃት ሊፈጸም የሚችለው። ስለዚህ ራሳችን ኃላፊነት ለመውሰድ ዝግጁ ነን” ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለለውጡ የተጠየቀውን ሰልፍ የከለከለው የክልሉ መስተዳድር በመስቀል አደባባዩ ሰልፍ በተከሰተው ፍንዳታ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች የሚጎበኙ ሹመኞችን ዛሬ ወደ አዲስ አበባ በመላክ የለውጡ ደጋፊ ለመምሰል የሚያደርገው ማጭበርበር እንዳበሳጫቸው አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል።
እንደ ሰልፉ አስተባባሪዎች ገለጻ፣ ብሄር ብሔረሰብን ለመወከል በሚል በክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ከሀረሪ ብሔራዊ ሊግ፣ ከኦህዴድ፣ ከብአዴንና ከህወኃት የተመረጡ የፕሬዚዳንቱ የቅርብ ሰዎች ናቸው ለተጎዱት ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ ተብለው ዛሬ ወደ አዲስ አበባ የተላኩት።
የክልሉ ርዕሰ ብሄርም እነሱን ተከትለው በነገው ዕለት ወደዚያ እንደሚያመሩ የውስጥ ምንጮችን ጠቅሰው የጠቆሙት ቄሮዎች፣ እያዬን የመጣነውን ብሩህ ለውጥ እንዳናወድስ እንቅፋት የፈጠሩብን ሹመኞች በጎን ወደ ማዕከል በመሄድ የለውጡ ደጋፊ ለመምሰል የሚያደርጉት ድብልቅ አሰላለፍ ሊጠራ ይገባል ሲሉ መክረዋል።