የቀድሞው የኢንሳ ዳሬክተር ዶ/ር ተክለብርሃን ወልደአረጋይ የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድን ጠላት ስለሆኑ ልንታገላቸው ይገባል ሲሉ ኮነኑ

የቀድሞው የኢንሳ ዳሬክተር ዶ/ር ተክለብርሃን ወልደአረጋይ የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድን ጠላት ስለሆኑ ልንታገላቸው ይገባል ሲሉ ኮነኑ
(ኢሳት ዜና ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ/ም) የቀድሞው የመረጃና ደህንነት ኤጄንሲ (ኢንሳ) ዳይሬክተር የነበሩት ዶክተር ተክለብርሃን ወልደአረጋይ በትግረኛ ቋንቋ ከሚተላለፈው ድምጸ ወያኔ ራዲዮ ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድን የለውጥ ጅምር አውግዘዋል። ‘“በዶክተር አብይ የሚመራው የለውጥ ኃይል ሳይሆን ጠላት ነው። በግልጽ ጠላት ብለን ካልፈረጅነው ልንታገለው አንችልም” ብለዋል።
በሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው በተፈቱት ዜጎችና በቅርቡ በመስቀል ዓደባባይ የተፈጸመውን ፍንዳታ አስመልክቶም “እኛው የመመርመር አቅም እያለን ለማጣራት የኤፍ.ቢ.አይ. መርማሪዎች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የአገርን ሉዓላዊነት የጣሰ ውሳኔ ነው።’’ ሲሉ እርምጃውን ኮንነዋል።
የኢንሳው ዳይሬክተር “እኛ ወንጀሉን የመመርመር አቅም አለን” ሲሉ መግለጻቸው በአገዛዙ ሰቆቃ እየፈጸሙ ምርመራ ስለሚያደርጉ መርማሪዎች ማለታቸው መሆን አለመሆኑን ግን ግልጽ አላደረጉም።
የአልጀርሱን ስምምነት ለመተግበር ዝግጁ መሆንን በመግለጽ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሰላም ለማስፈን የተሄደበትን የሰላም መንገድ የዶላርን እጥረት ለመቅረፍ እንደተደረገ ስሌት በመቁጠር ”የዶላር እጥረት አገርን በመሸጥ አይቀረፍም። የዶላር እጥረት የሚቀረፈው አገርን በማልማት ነው” በማለት የሰላሙን ውሳኔ እንደሚቃወሙትም ገልጸዋል።
ዶክተር ተክለብርሃን ወልደአረጋይ በቃለ ምልልሱ ዶክተር አብይን በብዙ ነገሮች የከሠሷቸውና የፈረጇቸው ሲሆን ፣ “ልንታገላቸው ይገባል” ሲሉም ጅምሩን ለውጥ ለመቀልበስና የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት ዳግም ለማጨለም ያላቸውን እቅድ በይፋ ተናግረዋል።